Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እና ጂቡቲ በቴሌኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ ያላቸውን አጋርነት ለማጠናከር ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ጂቡቲ በቴሌኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ ያላቸውን አጋርነት ለማጠናከር ተስማምተዋል፡፡

በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በጂቡቲ የስራ ጉብኝት ያደረገ ሲሆን፥ ሁለቱ ሃገራት በቴሌኮሙዩኒኬሽን መስክ ያላቸውን አጋርነት ለማጠናከር በሚረዱ ጉዳዮች ላይ ምክክር አድርጓል፡፡

በውይይቱ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የኢትዮጵያ መንግስት የቴሌኮም ዘርፍን ለማሻሻል እየወሰደ ስላለው እርምጃ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

እስከ አሁን ባለው ሂደትም በርካታ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኩባንያዎች ፍላጎታቸውን አሳይተዋል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ኢትዮ-ቴሌኮም ስትራቴጂካዊ አጋር እንዲኖረው 40 ከመቶ ድርሻውን ለሽያጭ እንዲያቀርብ መንግስት መወሰኑንና ለዚህም የዝግጅት እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቴሌኮም ዘርፍ እያደገ በሚመጣበት ወቅት ጂቡቲ በቴሌኮሙዩኒኬሽን መሠረተ ልማት ይበልጥ በመሳተፍ ተጠቃሚ እንደምትሆንና በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን የቴሌኮም ትራፊክ ደህንነት በማስጠበቅ ሂደት ውስጥ ጂቡቲ ወሳኝ ሚና ይኖራታል ማለታቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በጂቡቲ የፖስታ እና ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ሬድዋን አብዱላሂ ባህዶን በበኩላቸው የጂቡቲ መንግስት የቴሌኮም ዘርፉን በማጠናከርና በማዘመን ምስራቅ አፍሪካን የቴክኖሎጂ ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.