የሀገር ውስጥ ዜና

የገንዘብ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችና ቀጠናዊ ደህንነት ዙሪያ ከኢጋድ ዋና ፀሃፊ ጋር ተወያዩ

By Tibebu Kebede

March 15, 2021

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 6 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) በአባል ሃገራቱ ውስጥ ማሻሻያዎችን እና ተቋማዊ አቅምን ማጠናከር በሚቻልበት አግባብ ላይ ተወያዩ፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ከኢጋድ ዋና ፀሃፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሞች እና የአባል ሃገራቱን ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት አግባብ ላይ ተወያይተዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት በቀጠናው ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና በደህንነት ጉዳዮች ላይ ትስስርን በሚያጠናክር መልኩ ኢኮኖሚያዊ ትብብርን ማጎልበት አስፈላጊ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡

ትብብሩ ለሁሉም አባል ሃገራት ተጠቃሚነትና በተለይም ለአካባቢያዊ ሰላምና ደህንነት ወሳኝ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል፡፡

የኢጋድ ዋና ፀሃፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በበኩላቸው የኢጋድን ፕሮግራሞች በአግባቡ ለመተግበር ተቋማዊ አቅምን መገንባት ያለውን ጠቀሜታ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

አያይዘውም ተቋሙ ለቀጠናው እድገትና መረጋጋት ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት መስራቱን ይቀጥላልም ብለዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!