Fana: At a Speed of Life!

በባሌ፣ ቦረና እና ጉጂ ዞኖች የተከሰተውን የበርሃ አንበጣ ለመከላከል ተጨማሪ አውሮፕላኖች ወደ ስፍራው ይሰማራሉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል በባሌ፣ ቦረና እና ጉጂ ዞኖች የተከሰተውን የበርሃ አንበጣ ለመከላከል ተጨማሪ አውሮፕላኖች ወደ አካባቢዎቹ እንደሚሰማሩ ግብርና ሚኒስቴር ገለፀ።

ሚኒስቴሩ ካለፈው ሰኔ ወር ጀምሮ በኢትዮጵያ የተከሰተውን የበርሃ አንበጣ የመከላከል ስራ አሁንም ድረስ እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል።

መንጋው በኦሮሚያ ክልል በባሌ እና ቦረና ዞን ተከስቶ ጉዳት እያደረሰ ሲሆን፥ በደቡብ ክልል አዋሳኝ አጎራባች ወረዳዎች መንጋው ይዛመታል የሚል ስጋትንም አጭሯል።

የበርሃ አንበጣ በተከሰተባቸው የኦሮሚያ ዞኖች ከክልሉ ጋር በመቀናጀት በአውሮፕላን የኬሜካል ርጭት እየተካሄደ ቢሆንም በቂ ባለመሆኑ ከዛሬ ጀምሮ ተጨማሪ አውሮፕላኖችን ለመላክ መወሰኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት በሚኒስቴሩ የዕፅዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ዘብዲዮስ ሰላቶ የበርሃ አንበጣ መንጋውን የመከታተል እና የመከላከል ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ ያደገውና ከየመን እና ሶማሌ ላንድ በአፋር እና ሶማሌ ክልሎች በኩል ገብቶ አማራ፣ ትግራይ፣ ምስራቅ ኦሮሚያ እና ድሬዳዋ አካባቢ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ እስከ ህዳር ወር መጨረሻ ድረስ የመከላከላል ስራ የመጀመሪያው ምዕራፍ መሆኑንም ገልጸዋል።

በመከላከል ስራ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሌሎች አካባቢዎች የተሰደደው አንበጣ ከታህሳስ ወር በኋላ ዝናብ በሚያገኙ የሶማሌ ክልል ደቡብ ምስራቅ፣ ደቡብ ምስራቅ እና ደቡባዊ ኦሮሚያ፣ የደቡብ ክልል እንዲሁም ኬንያ እና ሶማልያ ይገባልም ነው ያሉት።

ከዚህ አንጻርም ችግሩ ድንበር ተሻጋሪ በመሆኑ የመከላከሉን ስራ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመሆን በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በስላባት ማናዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.