የኦሮሚያ፣ የአማራና አፋር ክልል ምክር ቤቶች የጋራ የምክክር መድረክ በሠመራ ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ጥር 5፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሚያ፣ የአማራና አፋር ክልል ምክር ቤቶች የጋራ የምክክር መድረክ በአፋር ክልል ሠመራ ከተማ ተካሄደ።
በዛሬው እለት የጀመረው የሶስቱ የክልል ምክር ቤቶች የምክክር መድረክ በአፋር ክልል ምክር ቤት አስተናጋጅነት ነው በመካሄድ ላይ የሚገኘው።
በምክክር መድረኩ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወርቀሰሙ ማሞ፣ የአፋር ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አሚና ሴኮ እና የጨፌ ኦሮሚያ ምክትል አፈ ጉባኤ መህቡባ አደም ተገኝተዋል።
ምክር ቤቶቹ በተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ መሠረት በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት፣ በግጭት መከላከል እና አፈታት እንዲሁም በአቅም ግንባታ ዙሪያ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የምክክር መድረክ አካሂደዋል።
በዛሬው የምክክር መድረክ እስካሁን በተከናወኑት የጋራ ተግባራት፣ ባጋጠሙ ችግሮች፣ መፍትሔዎቻቸውና በቀጣይ ስለሚከናወኑ ተግባራት በጋራ ተወያይተው አቅጣጫ ያስቀምጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ምንጭ፦ አብመድ