የፌዴራል መንግስት የልማት ፕሮጀክቶች አስተዳደር እና አመራር ረቂቅ አዋጅ የመንግስትን ሃብት ውጤታማ ዘርፎች ላይ ማዋል ያስችላል ተባለ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 6 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል መንግስት የልማት ፕሮጀክቶች አስተዳደር እና አመራር ረቂቅ አዋጅ የመንግስትን ሀብት በውጤታማ ዘርፎች ላይ ማዋል እንደሚያችል ተገለፀ፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 77ኛ መደበኛ ስብሰባው በፕላንና ልማት ኮሚሽን ተዘጋጅቶ የቀረበውን የፌዴራል መንግስት የልማት ፕሮጀክቶች አስተዳደር እና አመራር ረቂቅ አዋጅ መላኩ የሚታወስ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት መሰረታዊ የሆኑ አገልግሎቶችን ለህብረተሰቡ ለማድረስ ከፍተኛ ሀብት በመመደብ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ያከናውናል፡፡
ከዚህ ባለፈም ሀገሪቱ ከምትከተለው የልማት አቅጣጫ አንፃር በግሉ ዘርፍ ሊሞሉ የማይችሉ ዘርፎች ላይ መንግሰት በልማት ፕሮጀክቶች አማካኝነት የልማት ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡
ሆኖም የመንግስት ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸዉ መርኃ ግብር፣ የጥራት ደረጃ እና በጀት ባለመከናወናቸው በኢኮኖሚ ውስጥ ያመጣሉ ተብሎ የሚጠበቀውን ውጤት በሚጠበቀው ደረጃ ማግኘት እንዳልተቻለ የፕላንና ልማት ኮሚሽን ይገልጻል።
እነዚህን ተግዳሮቶች በጥልቀት ለመለየትም በፌደራል መንግስት የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ተከታታይ ጥናት መከናወኑ ተገልጿል፡፡
በተደረገው ጥናት በፕሮጀክት ዝግጅት ማለትም ከፕሮጀክት ጥናት፣ አመራረጥ እና ውሳኔ አሰጣጥ እንዲሁም በትግበራ ላይ የሚታዩ የፕሮጀክት ኮንትራት አስተዳደር፣ አፈፃፀም ክትትል እና የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን በውጤታማነት ማስተዳደር አለመቻል የሚሉ ችግሮች ተጠቅሰዋል።
እንዲሁም በፕሮጀክቶች ላይ ለታየው የወጪና የጊዜ መናር እንዲሁም የጥራት ችግር መንስኤዎች እንደነበሩ ተመላክቷል፡፡
በፕሮጀክት ዝግጅት እና ትግበራ ላይ የታዩ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ መከናወን ያለባቸው ማሻሻያዎችም ተለይተዋል።
በዚህም ከአሰራር አንፃር የሚታዩ የተጠያቂነት እና ግልፅነት ክፍተቶችን ለመፍታት በሚያስችል መልኩ የተለያዩ የፌደራል መንግስት አስፈፃሚ አካላት ያላቸውን ስልጣንና ሃላፊነት በሚያብራራ መልኩ የመንግስት ፕሮጀክቶች አስተዳደርና አመራር ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቷል።
በመሆኑም ይህ ረቂቅ አዋጅ የልማት ፕሮጀክቶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ተግባራዊ በማድረግ የሀገሪቱን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት ለማፋጠን እና የፌደራል መንግስት ፕሮጀክቶች የሚመሩበትን የአሰራር ስርዓት በህግ መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ ተጠቁሟል።
በዚህ ረቂቅ አዋጅ ውስጥ ስልጣን እና ሃላፊነት ያላቸው የመንግስት አካላት የተለዩ ሲሆን፥ እነዚህም የፌደራል መንግስት ፕሮጀክቶች አስፈፃሚ አካላት፣ የፕላንና ልማት ኮሚሽን፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ የፌደራል ግዥ ኤጀንሲ፣ የፌደራል መንግስት የተቀናጀ የመሰረተ ልማት ማስተባበሪያ እና የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ መሆናቸውን የፕላንና ልማት ኮሚሽን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጿል፡፡
መንግስት የሚያስቀምጣቸው የልማት ግቦችና አላማዎች በፕሮጀክቶች አማካኝነት የሚተገበር በመሆኑ የፕሮጀክቶቹ መነሻዎች እና ልየታ እነዚህን ግቦች የሚያሳኩ መሆናቸው በግልፅ በሚያመላክቱ ቁልፍ የውጤት አመላካቾች ሊረጋገጥ እንደሚገባ ኮሚሽነሯ ዶክተር ፍፁም አሰፋ ገልፀዋል፡