የአማራ ክልል የማህበረሰብ ተሳትፎ የተፋሰስ ልማት ንቅናቄ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል የማህበረሰብ ተሳትፎ የተፋሰስ ልማት ንቅናቄ በዛሬው እለት መጀመሩ ተገለጸ።
ንቅናቄው የፌደራልና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት በምዕራብ ጎጃም “የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ንቅናቄ ለምርት እድገት እና ለላቀ የህብረተሰብ ተጠቃሚነት” በሚል መሪ ቃል ተጀምሯል።
በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብትና የምግብ ዋስትና ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ካባ ኡርጌሳ ባለፉት አመታት በክልል በተሰሩ የተፈጥሮ ሃብት ስራዎች ለውጦች ተመዝግበዋል ብለዋል።
መንግስት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ አዋጅ እያዘጋጀ ነው ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው፥ ከአዳዲስ የተፋሰስ ግንባታ ባሻገር ነባር ተፋሰሶችን መጠገን እና መጠበቅ ይገባል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መለሠ መኮንን በበኩላቸው፥ በመክፈቻው ቀን ብቻ በክልሉ ሶስት ዞኖች እና 27 ወረዳዎች ወደ ስራ መግባታቸውን ጠቅሰዋል።
በዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ንቅናቄ ከ4 ሚለየን በላይ ሰወች እንደሚሳተፉ መግለጻቸውን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።