Fana: At a Speed of Life!

በአዲሱ የፈረንጆቹ ዓመት 1 ሺህ የሚጠጉ ወደ ሊቢያ መመለሳቸው ተነገረ

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በተያዘው አዲሱ የፈረንጆች ዓመት 1 ሺህ የሚሆኑ ስደተኞች ወደ ሊቢያ መመለሳቸውን ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት አስታወቀ።

የባህር ላይ ጠባቂዎች የሜዲትራንያንን ባህር ሲያቋርጡ የያዟቸውን ስደተኞች ወደ ሊቢያ መመለሳቸውን ድርጅቱ አስታውቋል።

ስደተኞቹ ከገባ ሁለተኛ ሳምንቱን በያዘው የፈረንጆቹ 2020 ብቻ የተያዙ ናቸው ተብሏል።

ከእነዚህ ውስጥ 136 ሴቶች ሲሆኑ 85 የሚሆኑት ደግሞ ህጻናት መሆናቸው ነው የተነገረው።

ከፈረንጆቹ 2011 ወዲህ ሰላም የራቃት ሊቢያ በተለይ አፍሪካውያን ስደተኞች ወደ አውሮፓ ለሚያደርጉት ጉዞ ዋነኛ መሸጋጋሪያ ሆና ታገለግላለች።

አሁን ላይ በሊቢያ ወደ 4 ሺህ 500 የሚሆኑ ሰዎች በተለያዩ እስር ቤቶች የሚገኙ ሲሆን፥ እስር ቤቶቹ ለእስረኞች ምቹ ያልሆኑና ከሰብዓዊ መብት አያያዝ አንጻር ቅሬታ የሚቀርብባቸው ናቸው።

ከዚህ ባለፈም ከግጭት ቀጠና ነጻ ያልሆኑና ከፍተኛ የደህንነት ስጋት የሚታይባቸው ናቸው።

ባለፈው አመት ታጁራ በተባለው አካባቢ በቦምብ ፍንዳታ 50 ስደተኞች ሲሞቱ፥ ከ130 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ቆስለዋል።

ከፈረንጆቹ 2016 ወዲህ ከ12 ሺህ በላይ ስደተኞች በሜዲትራንያን ባህር ወደ አውሮፓ ለመሻገር ሲሞክሩ ህይዎታቸውን አጥተዋል።

እንደ ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት አሁን ላይ በሊቢያ ከ636 ሺህ በላይ ስደተኞች ይገኛሉ።

ምንጭ፦ አልጀዚራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.