Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ የመከላከል ስራ እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥር 6 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሰኔ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገባ ከነበረው የአንበጣ መንጋ በተጨማሪ ከሶማሊያ እየገባ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ይህንንም ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል ባሌ ፣ ጉጂ ፣ ቦረና ዞኖች እንዲሁም በደቡብ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የበረሃ አንበጣ መከሰቱ ነው የተነገረው፡፡

የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል ተጨማሪ አራት አውሮፕላኖችን በመከራየት ለመራባት ምቹ በሆኑ ስትራቴጂክ ስፍራዎች ላይ ርጭት እየተካሄደ መሆኑን በሚኒስቴሩ የዕፅዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ዘብዲዎስ ስላቶ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

በተለይ ከሶማሊያ የሚመጣውን የበረሃ አንበጣ መንጋ ከጎዴና ድሬ ዳዋ ለመከላከል አውሮፕላኖች እና ባላሙያዎች እንደተሰማሩ ገልፀዋል፡፡

በአዲስ መልክ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ማለትም በባሌ ፣ጉጂ እና ሌሎች አካባቢዎች ህብረተሰቡ የአንበጣን ባህሪ እንዲረዳ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡

ወደ ሌሎች አካባቢዎች የአንበጣ መንጋው እንዳይዛመትም ከአውሮፕላን ርጭት በተጨማሪ የተቀናጅ የመከላከል ስራ እንደሚከናወን አቶ ዘብዲዎስ ገልፀዋል፡፡

ለአውሮፕላኖች ርጭት የማይመቹ አካባቢዎች ሲኖሩ እና አውሮፕላኖቹ ስራ ላይ በሚሆኑበት ወቅት የሚያመልጡ የአንበጣ መንጋዎች ካሉ ህብረተሰቡ በመጨፍጨፍ እና የመርጫ መሳሪያዎችን በመጠቀም የመከላከል ስራ እንዲያከናውን ጥሪ ቀርቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.