የሀገር ውስጥ ዜና

ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ የምርጫ ምልክቱን እና ማኒፌስቶውን ይፋ አደረገ

By Tibebu Kebede

April 09, 2021

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 1 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ ለስድስተኛው ዙር ሀገር አቀፍ ምርጫ የሚወዳደርበትን የምርጫ ምልክት እና ማኒፌስቶ ይፋ አድርጓል።

የነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር አብዱልቃድር አደም የፓርቲው ማኒፌስቶ የሀገሪቱን፣ የአህጉሩን ብሎም ዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታውን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በምርጫ ምልክት እና ማኒፌስቶ ማስተዋወቂያ መድረኩ ላይ የፓርቲው ራዕይ፣ ተልዕኮ እና ዓላማዎች ተዘርዝረዋል።

የፓርቲው ራዕይ አስተማማኝ ሰላምና ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገት የተረጋገጠባት፣ ዜጎች የዘር፣ የቋንቋ፣ የባህል፣ የሀይማኖት፣ የፖለቲካ አመለካከት ወዘተ ልዩነት ሳይደረግባቸው በብሔራዊ ጉዳዮች እኩል የሚሳተፉባት እና ከልማቷ እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑባት የበለጻገች እና ዴሞክራሲያዊት ሀገር እውን ሆና ማየት እንደሆነ ተገልጿል።

ተልእኮው ደግሞ፣ መልካም አስተዳደር እና የሕግ የበላይነት የተረጋገጠባት፣ የፖለቲካ ሥልጣን ከሕዝብ እና ከሕዝብ ብቻ የሚመነጭበት የፖለቲካ ባህል የዳበረባት፣ ዜጎች ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድሎችን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የሚጠቀሙባት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት መሆኑ ነው የተገለጸው።

ከፓርቲው ዓላማዎች መካከል፣ አካታች እና ዘላቂ ኢኮኖሚ በመገንባት ድህነትን መቀነስ ብሎም ማጥፋት፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፍትሕን ማስፈን፤ የሰብዓዊ እና ዴሞክራሲዊ መብቶች እንዲከበሩ ማድረግ፣ የሕግ የበላይነትን እውን ማድረግ እና ነጻ የፍትሕ ሥርዓት መገንባት፤ የብሔሮች እና ብሔረሰቦችን ቋንቋ እና ባህል በእኩልነት ለማበልጸግ፣ ሁሉንም የሀገራችንን ክልሎች ልማት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለማረጋገጥ የሚያስችል እውነተኛ የፌዴራል ሥርዓት መገንባት የሚሉ ይገኙባቸዋል።

የፓርቲው የምርጫ ምልክት ብዕር መሆኑን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!