የሀገር ውስጥ ዜና

የአዲስ አበባ ከተማ ከ29 ሺህ በላይ የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎችን አስመረቀ

By Tibebu Kebede

April 10, 2021

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 2 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ የምግብ ዋስትና እና ልማታዊ ሴፍቲኔት ኤጀንሲ ከ29 ሺህ 400 በላይ የልማታዊ ሴፍቲኔት ተጠቃሚዎችን አስመረቀ።

ኤጀንሲው የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት የልማታዊ የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች ወደ ተሻለ የስራ መስኮች መሸጋገራቸውን አስታውቋል።

በዚህም በአካባቢ ጥበቃ ስራ፣ በከተማ ግብርና እና በጽዳት አገልግሎት ስራ ላይ እንዲሰማሩ በማድረግ 29 ሺህ 410 በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረጉን ገልጿል።

ኤጀንሲው መርሃ ግብሩ ተግባራዊ ከተደረገበት ግንቦት ወር 2009 ዓ.ም ጀምሮ በሶስት ዙር ከ400 ሺህ በላይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ሆነዋልም ነው ያለው።

በመጀመሪያው ዙር ተጠቃሚ ከሆኑት ከ123 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ከ29 ሺህ በላይ የቤተሰብ ተወካይ በመምረጥ፥ የንግድ ስራ እቅድ በማዘጋጀት በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በተለያዩ ዘርፎች ስልጠና መውሰዳቸውን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አሳምነው ጌራወርቅ ገልጸዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ የተቋማት አገልግሎት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ ከተማ አስተዳደሩ የነዋሪዎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በሶስት ዓመት ውስጥ ከ400 ሺህ ተጠቃሚዎች መካከል 16 በመቶ የሚሆኑት የቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ መሆናቸውን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!