Fana: At a Speed of Life!

ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የስነ ምግባር ግድፈት በተገኘባቸው ተጨማሪ 52 ተማሪዎች ላይ እርምጃ ወሰደ

አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የስነ ምግባር ግድፈት ተገኝቶባቸዋል ባላቸው ተጨማሪ 52 ተማሪዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል።

የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ታህሳስ 27ቀን 2012 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በዩኒቨርሲቲው በተከሰተው የፀጥታ ችግር ላይ በተሳተፉ ተማሪዎች ላይ የስነ ምግባር እርምጃ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።

በዚህም የመማር ማስተማሩን ሂደት አስተጓጉለዋል የተባሉ 69 ተማሪዎች ጥፋታቸው በሂደት ተጣርቶ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ገልጾ ነበር።

ዩኒቨርሲቲው ጥር 6 ቀን 2012 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባም በዩኒቨርሲቲው እና በህግ አካላት በተለዩ 51 ተማሪዎች ላይ ውሳኔ አሳልፏል።

በዚህ መሰረትም 42 ተማሪዎች እያንዳንዳቸው የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ሲሆን፥ 7 ተማሪዎች ደግሞ እያንዳንዳቸው ለአንድ ዓመት እና 2 ተማሪዎች ለሁለት ዓመት ከትምህርት ገበታቸው እንዲታገዱ ተወስኗል።

ዩኒቨርሲቲው እስካሁን በአጠቃላይ የስነ ምግባር ችግር በታየባቸው 68 ተማሪዎች ላይ እንደ ጥፋታቸው መጠን የቅጣት ውሳኔ ማሳለፉን ከዩኒቨርሲቲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በተያያዘ ዜና የመቱ ዩኒቨርሲቲ ሴኔት ጥር 6ቀን 2012 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የመማር ማስተማር ሂደቱን አውከዋል ባላቸው 26 ተማሪዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል።

በዚህም 12 ተማሪዎች ለሁለት ዓመት፣ 6 ተማሪዎች ለአንድ ዓመት እንዲሁም 8 ተማሪዎች ሙሉ ለሙሉ ከትምህርት ገበታቸው እንዲታገዱ ውሳኔ አሳልፏል።

በቀጣይም በመሰል ድርጊቶች የተጠረጠሩ ተማሪዎች፣ መምህራን እና የአስተዳደር ሰራተኞችን አጣርቶ ተመሳሳይ የእርምት እርምጃ እንደሚወስድ ተመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.