የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ የወቅቱ አቋም በግድቡ ውሃ ሙሌት እና በሙሌቱ አስተዳደር ላይ ብቻ መነጋገር ነው – አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

By Tibebu Kebede

April 15, 2021

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 7 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የወቅቱ አቋም በግድቡ ውሃ ሙሌት እና በሙሌቱ አስተዳደር ላይ ብቻ መነጋገር መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ቃል አቀባዩ ባሳለፍነው ሳምንት የግድቡ ተደራዳሪ ሶስቱ ሃገራት ወደ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በማቅናት ያደረጉት ድርድር በፍላጎት መለያየት ሳቢያ ያለስምምነት መጠናቀቁን አስታውሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለድርድሩ ወደ ኪንሻሳ የሄደችው እንደተለመደው “የአፍሪካውያን ችግር በአፍሪካውያን ብቻ ይቀረፋል” በሚለው የዲፕሎማሲ መንገድ ማመኗን ለማረጋገጥ ነውም ብለዋል፡፡

ይህ ደግሞ “ወንዙም የአፍሪካውያን ነው” ከሚል የጋራ እሳቤ የሚመነጭ ነው ያሉት ቃል-አቀባዩ፥ ጉዳዩን ከአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ለማራቅ የሚደረገውን ጫና ኢትዮጵያ ፈፅሞ እንደማትቀበል ገልፀዋል፡፡

ሆኖም ግብፅ ራሷ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ከነበረችበት ወቅት ጀምሮ አሁን ህብረቱ በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ሊቀመንበርነት እስከሚመራበት ጊዜ ድርድሩን ወደራሷ ወደጅ ሃገራት ለማሸሽ እና የግል ጥቅሟን ለማስከበር ወደሚያግዟት ተቋማት ለመሳብ ያልሞከረችው መንገድ አልነበረምም ነው ያሉት አምባሳደር ዲና፡፡

ኢትዮጵያም ይህን አመለካከት ብቻ ሳይሆን “ሌሎች ወገኖችም የአፍሪካን ያህል በግድቡ ድርድር ላይ ሚና ይኑራቸው” የሚለውን ፍላጎት እንኳን እንደማትቀበል አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ከሱዳን ጋር በተያያዘም በተለይም የሱዳን ወታደራዊ ክንፍ የውክልና ተልዕኮ ይዞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሯ አብደላ ሃምዶክ በኩል የቀረበውን “በዝግ የእንነጋገር” ጥያቄ ኢትዮጵያ በአንክሮ እንደምትመለከተውም ጠቅሰዋል፡

ሱዳን ከድንበር ግጭት ጋር በተገናኘ በኢትዮጵያ ላይ የፈፀመችውን የመሬት ወረራ እና የንብረት ጉዳት በተመለከተ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና ወዳጅ ሃገሮቿ ተፅዕኖ በመፍጠር ወደ ቀደመው የግንኙነት መንገዷ እንድትመለስ እንዲያደርጉ ኢትዮጵያ ጥሪ እያስተላለፈች መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

በትግራይ ክልል ካለው ሰብዓዊ ድጋፍ ጋር በተያያዘም ድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቅሰው፥ “መንገድ ክፈቱልን” ሲሉ የነበሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት መንገድ ሲከፈት ከአሜሪና ከተወሰኑ ሃገራት ውጪ ባዶ እጃቸውን መሆናቸውን መመልከት እንደተቻለ አስረድተዋል፡፡

በሶዶ ለማ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!