የሀገር ውስጥ ዜና

ኮሚቴው የተከናወኑ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ አሰጣጥ ተግባራትን ገመገመ

By Tibebu Kebede

April 15, 2021

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 7 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ሰጭ የሚኒስትሮች ኮሚቴ በሁሉም ሀገሪቱ ክፍሎች የተከናወኑ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ አሰጣጥ ተግባራትን ገመገመ።

በሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ሰብሳቢነት በተካሄደው ግምገማ በመላ ሀገሪቱ ሊከሰቱ የሚችሉ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች ከመከሰታቸው አስቀድሞ ለመከላከል እንዲቻል የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ የሚሹ ጉዳዮች ላይ ቅድመ ግምት የዳሰሳ ጥናት ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

ለተገማች ችግሮች የተቀናጀና ጠንካራ ምላሽ መስጠት እንዲቻል ከተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተውጣጣ የአደጋ ቅድመ-ግምትና ፈጣን ምላሽ አሰጣጥ ተግባራትን የሚያቅድና በየስፍራው በመገኘት የሚያስተባብር የባለሙያዎች ቡድን መሰየሙ ተገልጿል።

ኮሚቴው በሪፖርቱ የቀረቡ አመላካች ሁኔታዎች ላይ በዝርዝር ተወያይቶ እስከ አሁን በቅንጅት እየተከናወኑ ካሉ አበረታች ተግባራት ልምድ ተወስዶ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

ከዚህ ባለፈም በቀጣይ ከወረዳ እስከ ፌደራል በየደረጃው ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን በጋራ ቀድሞ መከላከል የሚያስችል የአሰራር አደረጃጀት እና ፈጣን ምላሽ የመስጠት ሂደት ላይ ተጨማሪ አቅጣጫ ማስቀመጡን ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!