Fana: At a Speed of Life!

ሳዑዲ ሕጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ ሳያሳድሱ የቆዩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ለመመለስ ይጠየቁ የነበረውና የመውጫ ቪዛ ውዝፍ መቀጮ ክፍያን አነሳች

አዲስ አበባ ፣ ጥር 7፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙና ሕጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ ሳያሳድሱ የቆዩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ለመመለስ በቤተሰብ አባላት ቁጥር በነፍስ ወከፍ ይጠየቁ የነበረውና የመውጫ ቪዛ ውዝፍ መቀጮ ክፍያ እንዲነሳ ከሀገሪቱ መንግስት ጋር ከስምምነት ተደረሰ።
 
ሕጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ ሳያሳድሱ በሳዑዲ ዓረቢያ በቆዩ የሁሉም የውጭ አገር ዜጎች ላይ እየተተገበረ የሚገኘውና የመውጫ ቪዛ ለማግኘት በቤተሰብ አባላት ቁጥር በነፍስ ወከፍ በየወሩ ይጠይቅ የነበረው 400 የሳዑዲ ሪያል ውዝፍ መቀጮ ክፍያ በመብዛቱ ምክንያት በርካታ ዜጎች ከዕድሉ ተጠቃሚ ሳይሆኑ መቅረታቸውን አስታውሷል።
 
ኤምባሲውም ይሀው ክፍያ እንዲቀንስ ወይም እንዲነሳ ባቀረበው ጥያቄ ላይ ከሳዑዲ ዓረቢያ የመንግስት አካላት ጋር በተደረገ ውይይትና ግፊት የውዝፍ ክፍያው ሙሉ በሙሉ እንዲነሳ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ጋር ከስምምነት መደረሱን አስታውቋል።
 
ይህ ስምምነት በዋናነት በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙና ሕጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ ሳያሳድሱ
ለቆዩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ ዓረቢያ ሮያል ኮርት በተሰጠ ምህረትና መመሪያ በልዩ ሁኔታ የተፈቀደ ነው ብሏል።
 
ተግባራዊ የሚሆነውም በመጪዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ባለው ጊዜ ብቻ እንደሆነም ነው ያስታወቀው።
 
ይህንኑ የአጭር ጊዜ ዕድል ለዜጎች ለማዳረስ እንዲቻል ከሪያድ የኢፌዲሪ ኤምባሲና ጅዳ ቆንስላ ጽ/ቤት በተጨማሪ በመዲና፣ አብሃ፣ ጂዛን፣ ጣኢፍ ከተሞች ጭምር የጊዜያዊ አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎቸ ተከፍተው ሂደቱን ለማስጀመር ከሚለከታቸው የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት መስሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር ቅድመ ዝግጅት በመደረግ ላይ እንደሚገኝም ነው ያመለከተው።
 
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዜጎችን የጉዞ ሂደታቸውን ከማጠናቀቃቸው በፊት በስማቸው የተመዘገበ ተሽከርካሪ ካለ ወደ ትራፊክ ቢሮ በመሄድ ሃላፊነት ማውረድና በግላቸው የጉዞ ቲኬት የማዘጋጀት ሃላፊነት መወጣት ይኖርባቸዋል ብሏል።
 
በመሆኑም በዚህ በመጪዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ባለው ጊዜ ብቻ ተፈጻሚ የሚሆነውን እድል ዜጎችን በአግባቡ እንዲጠቀሙበት ኤምባሲው ያሳሰበ ሲሆን፥ ከሳዑዲ ዓረቢያ የፖሊስ፣ ሕግ አስፈጻሚና ጸጥታ አካላት ጋር በተደረገ ምክክር ዜጎችን አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ ጣቢያዎቹ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት አላስፈላጊ እንግልት እንዳያጋጥማቸው ሁኔታዎች የተመቻቹ መሆኑንም አስታውቋል።
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.