የሀገር ውስጥ ዜና

ከተለያዩ ክልሎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በአማራ ክልል ለሚገኙ ዜጎች የዕለት ምግብ እርዳታ እየቀረበ መሆኑ ተገለጸ

By Meseret Awoke

April 21, 2021

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ከተለያዩ ክልሎች ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የዕለት ምግብ እርዳታ እየቀረበ መሆኑን የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታውቋል።

በተለያዩ ክልሎች በተፈጸመባቸው ጥቃት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ ወገኖች የእለት ምግብ እርዳታ እየቀረበ ነው ተብሏል።

የፌደራልና የክልል መንግስታት ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባልም ብሏል ኮሚሽኑ።

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም እንደገለጹት፤ በተለያዩ ክልሎች ውስጥ በተፈጸመባቸው ጥቃት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ግማሽ ሚሊየን የሚሆኑ ወገኖች ወደ ክልሉ በመምጣት ተጠልለው ይገኛሉ።

በተጨማሪም ሰሞኑን በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በአጣየ፣ ሸዋሮቢትና አካባቢዎቻቸው በተፈፀመ ጥቃት ከ200 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን ተናግረዋል።

“በጥቃቱ የሰዎች ህይወት ጠፍቷል፣ ከፍተኛ የሆነ ንብረት ወድሟል፣ በተፈናቀሉ ወገኖች ላይም ከፍተኛ የሆነ የስነ ልቦና፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ደርሷል” ብለዋል ኮሚሽኑ ።

በአማራ ተወላጆች ላይ በየአካባቢው እየደረሰ ያለው ጥቃት በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው፤ ሁኔታው በክልሉ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን ማመላከታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ የልማት ድርጅቶችን በማስተባበር ለተፈናቃዮች በየወሩ እስከ 60 ሺህ ኩንታል እህል ድጋፍ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ህብረተሰቡንና ባለሃብቶችን በማስተባበር የእለት ደራሽ ምግብ እንዲያገኙ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፦https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!