ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ከማሳቹሴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ ጋር በትብብር ለመሥራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 8 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ከአሜሪካው ማሳቹሴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ ጋር ጋር በትብብር ለመሥራት የሚያስችል የውል ስምምነት ተፈራረመ።
ስምምነቱ በኮምፒዩቲንግና ኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ የሚሰጡትን የትምህርት ፕሮግራሞች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በታገዘ የቤተ ሙከራ ትምህርት ለማስደገፍ የሚያስችል መሆኑን በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሐብቴ ዱላ ገልጸዋል።
ዶክተር ሐብቴ ኢንስቲቲዩቱ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በገባው ውል መሰረት ከያዝነው የትምህርት ዘመን ሁለተኛው መንፈቅ ዓመት ጀምሮ አመታዊ ክፍያው ከ160 ሺህ ብር በላይ የሆነውን የኦንላይን ትምህርት በነጻ መስጠት ይጀምራል ብለዋል።
ለዚህ እቅድ ተግባራዊነት ኢንሰቲቲዩቱ ድጋፍ ሰጭ ቡድን ወደ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በመላክ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛልም ነው ያሉት።
ድጋፍ ሰጭ ቡድኑ የኦንላይን ትምህርቱን ለመስጠት ወሳኝ የሆኑ የቤተ ሙከራ ቁሳቁሶችን ይዞ በመምጣት ለዩኒቨርሲቲው በእርዳታ ማበርከቱንም አስረድተዋል።
ሁለቱ ተቋማት በጋራ መስራት እንዲችሉም በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
ሁለቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የገቡትን ውል በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር ለማሸጋገር የሚያስችላቸውን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ማከናወን መጀመራቸውንም ከዩኒቨርሲቲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።