Fana: At a Speed of Life!

ለምርጫው ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊነት ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው – የፌዴሬሽን ምክር ቤት

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 18 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሐዊ ሆኖ እንዲከናወን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጠየቀ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አደም ፋራህ፣ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊ እና በሕዝብ ዘንድ ተዓማኒነት ያለው እንዲሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ለምርጫው ሂደት ስኬታማነት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሚያከናውናቸው ልዩ ልዩ ተግባራት በተጨማሪ መንግሥት እንዲሁም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አንስተዋል።

የፌዴራል እና የክልል መንግሥታትም ይህን ተገንዝበው የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ-መንግሥቱ የበላይ ጠባቂ እንደመሆኑ ምርጫ ሕገ-መንግሥቱ ባስቀመጠው አግባብ እንዲሄድ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱንም አብራርተዋል።

በምርጫው የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጭ ሐሳባቸውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለሕዝብ በማቅረብ ድምፅ ለማግኘት መፎካከር ይገባቸዋልም ነው ያሉት።

ምርጫውን በማሸነፍ ወደ ሥልጣን የሚመጣው አካል ደግሞ ለሕዝቡ ቃል የገባውን በአግባቡ ለመፈጸም እና የሕገ-መንግሥቱን የበላይነት ማስከበር ይጠበቅበታል ብለዋል።

ሀገርን ማሻገር የሚቻለው የፉክክር እና የትብብርን ሚዛን ጠብቆ በመሔድ መሆኑን አስገንዝበው፣ ከዚህ አንጻር እንደ ሀገር የጋራ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ በትብብር መሥራት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።

ዜጎች ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ በመውሰድ እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ በምርጫው በመሳተፍ ሕገ-መንግሥቱ ያጎናጸፋቸውን መብት እንዲጠቀሙም ጥሪ አቅርበዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.