የሀገር ውስጥ ዜና

በጎባ ሪፈራል ሆስፒታል “ዶክተር ነኝ” በማለት ሲያጭበረብር የተገኘ ግለሰብ በእስራትና በገንዘብ ተቀጣ

By Meseret Awoke

April 28, 2021

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የጎባ ወረዳ ፍርድ ቤት በጎባ ሪፈራል ሆስፒታል “የህክምና ዶክተር ነኝ” በማለት በተደጋጋሚ ህብረተሰቡ ላይ የማጭበርበር ወንጀል ፈጽሟል ያለውን ግለሰብ በ6 ዓመት ከ6 ወር እስራትና በገንዘብ ቀጣ።

ፍርድ ቤቱ ዛሬ በዋለው ችሎት የቅጣት ውሳኔውን ያሳለፈው በጎባ ከተማ ኦዳ በሃ ቀበሌ ነዋሪ በሆነው አብዱልጀዋድ አማን ላይ ነው።

ግለሰቡ በተደጋጋሚ በጎባ ሪፈራል ሆስፒታል የህክምና ባለሙያዎችን የደንብ ልብስ በመልበስ በሰራቸው የማጭበርበር ወንጀሎች መከሰሱ በችሎቱ ተመልክቷል።

ግለሰቡ ሚያዝያ 13 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ አራት ሰዓት አካባቢ በሆስፒታሉ ጊቢ ውስጥ አቶ አልይ ሶሞ የተባሉ የግል ተበዳይን “የተሻለ መድኃኒት በእኔ ክሊኒክ ውስጥ ይሸጣል” በማለት 3 ሺህ 460 ብር ተቀብሎ መሰወሩን ተበዳዩ ለፖሊስ በሰጡት ቃል መረጋገጡን የፍርድ ቤቱ ዳኛ አቶ ተማም ጁንዲ በችሎቱ ላይ አሰምተዋል።

ግለሰቡ በተጨማሪም በተጠቀሰው ሆስፒታል ሚያዝያ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ አምስት ሰዓት አካባቢ አቶ አህመድ አብዱላሂ የተሰኙ የግል ተበዳይን 8 ሺህ ብር ለመቀበል እያስማማ ባለበት ሁኔታ ማንነቱን ለማረጋገጥ ባደረጉት ጥረት ጥርጣሬ ስላደረባቸው ለጎባ ከተማ ፖሊስ በሰጡት ጥቆማ እጅ ከፍንጅ መያዙን ዳኛው አመልክተዋል፡፡

“ተከሳሽ በፖሊስ በተያዘበት ወቅት 18 ሲም ካርድ፣ ሁለት ዘመናዊ የተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ ቀፎዎችና 10 ሺህ 630 ብር በማስረጃነት ተገኝቶበታል” ብለዋል ዳኛው።

ግለሰቡ ድርጊቱን አለመፈጸሙንና የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ በሰጠው የእምነት ክህደት ቃል መግለጹን ኢዜአ ዘግቧል።

በመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ተወካይ ዶክተር አቡበክር መሐመድ፤ ሆስፒታሉ ከባለሙያዎች የደንብ ልብስና ከባጅ አጠቃቀም ጋር የሚስተዋሉ ጉድለቶችን እንደሚያይ ገልጸዋል።

ለወደፊቱ ለጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ የተናገሩት ዶክተር አቡበክር፤ ህብረተሰቡም ከደረሰኝ ውጭ የሚደረጉ ክፍያዎችን እንዳይቀበልና በመድኃኒት እጥረት ምክንያት ከሆስፒታሉ ውጭ እንዲገዙ ሲታዘዙ በጥንቃቄ እንዲገዙ መክረዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!