ለትግራይ ክልል 371 ሚሊየን ብር ወጪ የተደረገባቸው መድኃኒቶችና ሌሎች የህክምና ቁሳቁሶች ቀርበዋል
አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 21 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በትግራይ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት በ371 ሚሊየን ብር ወጪ የተደረገባቸው መድኃኒቶችና ሌሎች የህክምና ቁሳቁሶችን ማቅረቡን የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ገለጸ።
የኤጀንሲው ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ ለኢዜአ እንደገለጹት÷ በትግራይ ክልል የመድሃኒት አቅርቦት እንዳይስተጓጎል ከፍተኛ ትኩረት ተደርጓል።
በክልሉ የጸጥታ ችግር ከተከሰተ በኋላ ከህዳር ወር ጀምሮ ቅርንጫፎች ሥራ መጀመራቸውን ተከትሎ የመድሃኒቶች አቅርቦት እየተደረገ መሆኑን ነው የገለጹት።
ኤጀንሲው ለክልሉ መድሃኒትና ሌሎች ቁሳቁሶችን ለማቅረብ በመቀሌና በሽሬ ካሉት ቅርንጫፎች በተጨማሪ ያጎራባች የጎንደርና የደሴ ቅርንጫፎችን መጠቀሙን ተናግርዋል።
ይህንንም ተከትሎ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 371 ሚሊየን ብር ወጪ የተደረገባቸ መድኃኒቶችና ሌሎች የህክምና ቁሳቁሶች ለክልሉ መቅረቡን ገልጸዋል።
ከእነዚህም 181 ሚሊየን ብር ወጪ የተደረገባቸው መድሃኒቶችና ሌሎች የህክምና ቁሳቁሶች ለጤና ተቋማት መሠራጨታቸውን ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት።
በቀጣይ ቀሪዎቹ መድሃኒቶችና ሌሎች የህክምና ቁሳቁሶችም ከተከማቹበት ማዕከል ወደ ተለያዩ የጤና ተቋማት በቅርቡ እንደሚሰራጩ ተናግረዋል።
ጎን ለጎንም የክልሉን ጤና ተቋማት መልሶ ለማቋቋም የተለያዩ ድጋፎችን በማሰባሰብ ጭምር ወደ ክልሉ መላኩን ነው ዳይሬክተር ጀነራሉ ያብረሩት።
በሌላ በኩል ኤጀንሲው የኮሮናቫይረስ ክትባት ወደ አገር ከገባ በኋላ በጥንቃቄ ለማከማቸትና ለማዘዋወር ለወራት ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ጠቅሰዋል።
ኤጀንሲው ባሉት ሁሉም ቅርንጫፎች ክትባቶቹን ለማስቀመጥ የሚያስችሉ አዳዲስ ማቀዝቀዣዎች መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል።
በተጨማሪም 17 ማቀዝቀዣዎች ለክትባቱ ሥርጭት ተዘጋጅተው መመደባቸውን ተናግረዋል።
በዚህም እስካሁን ወደ አገር ከገባው 2 ነጥብ 2 ሚሊየን አስትራ ዜኒካ ክትባት 2 ነጥብ 1 ሚሊየን ክትባት ከሶማሌ ክልል 5 ወረዳዎችና ከመተከል ዞን ውጭ በሁሉም የአገሪቱ አከባቢዎች መሰራጨታቸውን ገልጸዋል።
ከቻይና የገባው 300 ሺህ የሲኖ ፋርም ክትባትም አሁን ላይ በአዲስ አበባ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና ለከተማ አውቶብስ አሽከርካሪዎች እንዲውል እየተሰራጨ መሆኑን ተናግረዋል።
ኤጀንሲው ከዚህ በኋላ የሚመጡትን ክትባቶች በቀዝቃዛ ስፍራ የማስቀመጥ ሰንሰለትን ተጠቅሞ በማከማቸት ለማከፋፈል መዘጋጀቱን ዶክተር አብዱልቀድር መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!