Fana: At a Speed of Life!

በሊቢያ ያለው ግጭት እንዲያበቃ የአውሮፓ ህብረት ቱርክን እንዲደግፉ  ኤርዶኻን  ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ጥር 9፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) በሊቢያ ያለው ግጭት እንዲያበቃ የአውሮፓ ህብረት ቱርክ በሀገሪቱ እያደረገች ያለውን እንቅስቃሴ እንዲደግፉ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይፕ ኤርዶኻን ጥሪ አቀረቡ፡፡

በሊቢያ ያለውን ግጭት ለማስቆም ከተፈለገ ቱርክ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ህጋዊ እውቅና ላለው መንግስት የምታደርገውን ወታደራዊ ድጋፍ አውሮፓም እንድትደግፍ ጥሪ ማቅረባቸው ተነግሯል፡፡

ኤርዶኻን አያይዘውም በተመድ ህጋዊ እውቅና ያለው የፋይዝ አል ሳራጅ አስተዳደር ከወደቀ አል ቃይዳና አይ ኤስ የመሰሉ የሽብር ቡድኖች በአካባቢው ምቹ ሁኔታ ሊፈጠርላቸው ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡

አውሮፓ በሊቢያ ወታደራዊ ድጋፍ ለማድረግ እምብዛም ፍላጎት የላትም ካልን የመጀመሪያው አማራጭ በሊቢያ ወታደራዊ ድጋፍ ለመስጠት ቃል ከገባችው ቱርክ ጋር በጋራ መስራት ነው ብለዋል ፕሬዚዳንቱ፡፡

የሊቢያ የፀጥታ ኃይሎችን በማሠልጠን ሽብርተኝነትን ፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን እና በዓለም አቀፍ ደህንነት ላይ ስጋት የሆኑ ሌሎች አሳሳቢ አደጋዎችን በመዋጋት እናግዛቸዋለን ብለዋል፡፡

ኤርዶኻን ጥሪውን ያቀረቡት ሀገሪቱን ለማረጋጋት በነገው ዕለት በጀርመን በበርሊን ከሚካሄደው ስብሰባ አንድ ቀን ቀደም ብለው ነው፡፡
በስብሰባው ላይ ጀርመን እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጄኔራል ሃፍታርና የሊቢያ ጦር ሀይል በዋና ከተማዋ ትሪፖሊና አካባቢዋ ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት ለማስቆምና ወደ ሰላም ለማምጣት ግፊት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ነገር ግን በሁለቱ ወገኖች መካከል የኃይል መጋራት እንዲኖር ምንም አይነት ሙከራ እንደማይደረግ ነው የተነገረው፡፡

በፈረንጆቹ 2011 ከሙዓመር ጋዳፊ ህልፈት በኋላ ወደ ብጥብጥ የገባችውን ሊቢያን ወደ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት በሚደረገው ጥረት መካከል በተመድ

ህጋዊ እውቅና ያለው የፋይዝ አል ሳራጅ አስተዳደር እና ተቀናቃኙ ጀኔራል ከሊፋ ሃፍታር በርሊን እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

የቱርክ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይፕ ኤርዶኻን፣የሩስያ አመራሮች፣ ግብጽ እና ሌሎች የምዕራባዊ እና የአረብ ኃይሎች በበርሊን በሚካሄደው ውይይት ይሳተፋሉ፡፡

ምንጭ፡- ሮይተርስ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.