የሀገር ውስጥ ዜና

የአፍሪካ ልማት ፈንድ በኢትዮጵያ ለህጻናት የተመጣጠነ ምግብ ለማቅረብ 31 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አፀደቀ

By Tibebu Kebede

May 03, 2021

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 25፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአፍሪካ ልማት ፈንድ በኢትዮጵያ ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት የተመጣጠነ ምግብ ለማቅረብና መቀንጨርን ለመከላከል 31 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አፀደቀ።

ድጋፉ ከአምስት ዓመት በታች ለሆናቸው ህፃናት የሚቀርበውን ዘርፈ ብዙ የተመጣጠነ ምግብ ለማሳደግ ያለመ መሆኑን ፈንዱ አስታውቋል።

ድጋፍም ጤናን ለማሻሻል ፣ የተለያዩ የተመጣጠኑ የምግብ አይነቶችን ለማቅረብ፣ በህጻናት አመጋገብ ዙሪያ እውቀት እና አመለካከትን ለማሻሻል እንዲሁም ጡት ማጥባትን ፣ እንክብካቤን እና ንፅህናን ለማሳደግ የሚያግዝ መሆኑን ባንኩ ገልጿል።

ፕሮጀክቱ በአማራ እና ትግራይ ክልሎች በሚገኙ 40 ወረዳዎች ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑም ተጠቁሟል።

ይህ ፕሮጀክት የተመጣጠነ የምግብ አቅርቦቱን ውጤታማ ለማድረግ የአየር ንብረት ለውጥን ታሳቢ ያደረገ መሰረተ ልማትን መገንባት ፣ የቤተሰብ ድጋፍ ፣ የተመጣጠነ ምግብ ምርትን ማስተዋወቅ እንዲሁም ተቋማዊ ስርዓትን ማጠናከር እና አቅም ግንባታ ላይ ያተኮረ መሆኑም ተገልጿል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!