የሕግ ማሻሻያዎች ባለፉት ሦስት ዓመታት ለተሰሩት ሥራዎች ምሰሶዎች ናቸው – ጠ/ሚ ዐቢይ
አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሕግ ማሻሻያዎች ባለፉት ሦስት ዓመታት ለተከወኑት የኢትዮጵያ የብልጽግና ራዕይ ሥራዎች ምሰሶዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ፥ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አይነት የዴሞክራሲና የፍትህ ተቋማትን ነጻነት ለማረጋገጥ ሰፊ የማሻሻያ ተግባራት መከናወናቸውን አስታውቀዋል፡፡
በተጨማሪም የዜጎች መሰረታዊ መብቶች እና ነጻነቶች የሆኑት የመደራጀት፣ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽና ነጻ ፖለቲካዊ ተሳትፎን የማድረግ መብቶችን የሚያስከብሩ የህግ ማዕቀፎች መፅደቃቸውንና ተግባራዊ መደረጋቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የመንግስትን አሰራር ግልጽነትና ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የሚረዳ የፌደራል አስተዳደር ስርአት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 ፀድቆ ተግባራዊ መደረጉን ጠቅሰው፥ የወንጀል ፍትህ ስርአቱን ለማዘመንና ለማሻሻል የሚረዳውን አዲሱ የወንጀል ህግ ስነ ስርአት እና የማስረጃ ህግ መድብል መፅደቁንም ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም አዲሱ የንግድ ህግ መድብል እና የግልግል ዳኝነትና እርቅ አሰራር ስነ ስርአት አዋጅ መጽደቁንም አንስተዋል፡፡
ከሙስና ጀምሮ ማንነትን መሰረት እስካደረገ ጥቃት ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪዎችን በመለየት ለህግ ማቅረብ መቻሉን በመጥቀስም፥ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በመላ ሃገሪቱ ከ45 ሺህ በላይ ዜጎች ምህረትና ይቅርታ ተደርጎላቸው ከማረሚያ ቤት መውጣታቸውንም አውስተዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!