ለከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች የማዕረግ ሹመት ተሰጠ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 9፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ለከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች የማዕረግ ሹመት የመስጠት ማእረግ የማልበስ ስነ ስርዓት ተከናወነ።
በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር ዐቢይ አህመድ አቅራቢነት በኢፊዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የማዕረግ ሹመቱ የተሰጠው።
የማዕረግ ሹመት አሰጣጡ ላይ ንግግር ያደረጉት የጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር ዐቢይ አህመድ “በሀገሩ የሚኮራ፤ ሀገሩን የሚያኮራ፤ ለዘመናት ጀግንነቱን ያስመሰከረ፤ ድል ማድረግ ዜማው ፤ ማሸነፍ ቋንቋው የሆነ፤ የራሱን የማይሰጥ የሰውን የማይወስድ፤ የአፍሪካ ኩራት የኢትዮጵያ መከታ እንዲሁም ሰላምን ከፍ ለማድረግ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ” ብለውታል የኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊትን።
መከላከያ ሰራዊቱ በውስጥ ሰላምና ደህንነትን በውጪ ድንበርና ሉዓላዊነትን እያስከበረ ይገኛል ብለዋል የጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዡ።
ከድሆች ጓዳ እስከ ገበሬው ሰብል አጨዳ ተሰማርቶም የሚገኝ ጀግና ሰራዊት መሆኑንም አንስተዋል።
ምትክ ለሌላት ሀገራቸው ግንባራቸውን የሚሰጡ ጅግኖችን ሀገሪቱ ማፍራት ቀጥላለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ ዛሬም ለሹመት የበቁት ወታደራዊ አመራሮች ለዚህ አብነት መሆናቸውን አንስተዋል።
በዛሬው ወታዳራዊ ሹመት አሰጣጥ የሴቶችን አኩልነት ለማሳደግ ለሴት ወታደራዊ አመራሮች ሹመት እንደተሰጣቸውም ተናግርዋል።
ወታዳራዊ ሹመቱም ተዋፅዕዎን የጠበቀ መሆኑንም ገልፀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው መከላከያ ሰራዊቱ የሚቆመው ለህገ መንግስቱ መርሆች መከበር ብቻ መሆኑን በማንሳት ሁሉንም በእኩልነት ነፃ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።
በሀገሪቱ የብሄረሰብም የሃሳብም ብዝሃነት የሚኖር መሆኑን የሚያውቅ ሰራዊት በመገንባት ላይ እንገኛለንም ነው ያሉት።
ማንኛውም ነገር ከሀገር ሉዓላዊነት አይበልጥም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የፓለቲካ ሀይሎች ህገ መንግስቱን አክብረው መንቀሳቀስ ግዴታቸው መሆኑን አስታውቀዋል።
ጀነራል መኮነኖች በውሏቸውና በስራቸው እንደሚመዘኑ በማንሳትም ውሏቸውና ስራቸውን እንዲያሳምሩ አሳስበዋል።
የኢፌዴሪ መከላከለያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል አደም መሀመድ በበኩላቸው ሰራዊቱ የሀገር ሉዓላዊነት፣ ሰላምና ደህንነትን በማስጠበቅ ህገ መንግስታዊ ተልዕኮውን እየተወጣ መሆኑን ገልፀዋል።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ሁልጊዜ ውግንናው ለህዝብ በመሆኑ በተሰማራባቸው ግዳጆች ሁሉ ውጤታማ ሆኖ መዝለቁንም ገልፀዋል።
የዛሬው ሹመት የተሰጣቸው ወታደራዊ መኮንኖች በነበራቸው ሃላፊነት፣ ባስመዘገቡት አፈፃፀም እና በቀጣይም የላቀ ውጤት ያስመዘግባሉ በሚል እምነት መሆኑንም ነው የተናገሩት።
በዚህም በአጠቃላይ ለ65 ጄኔራል መኮንኖች የማዕረግ ሹመቱ የተሰጠ ሲሆን ስድስቱ የሌትናል ጀነራል፣ 19 ሜጀር ጀነራልና 40ዎቹ ደግሞ የብርጋዴር ጀነራልነት ማዕረግ የተሰጣቸው ናቸው።
የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ለማ መገርሳ እንደገለፁትም በመከላከያ ሰራዊት ውሰጥ እየተከናወነ ያለው ሪፎርም ሰፊና ጥልቅ ለውጥም እያመጣ ይገኛል።
በሪፎርሙ ሙለ በሙሉ የመከላከያን አደረጃጀት ከማስተካከል በለፈ በየጊዜው ይነሳ የነበረውን የደሞዝና የጥቅማጥቅም ጥያቄ ምላሽ መስጠት የቻለም ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጠብቀው የመከላከያ ሰራዊት የተሟላ አደረጃጀት እንዲኖረው ባህር ኃይል እሰከ ማቋቋም ድረስ መኬዱንም ነው ያነሱት።
ከዓለምአቀፍና አካባቢያዊ ሁኔታ ጋር አብሮ መሄድ የሚችል የዘመነ መከላከያ ሰረዊት ለመገንባት ወታደራዊ ኮሌጆችን የመክፈትና የተከፈቱትንም የማጠናከር ስራ መከናወኑንም አቶ ለማ አስታውቀዋል።
የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ከመቼውም ጊዜ በላይ ህብረብሔራዊነቱን ጠብቆ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ እንዲያደርግ አመለካከት ላይ መሰራቱን ተናግረዋል።