የበልግ ዝናብ በአንዳንድ አካባቢዎች ጎርፍ ሊያስከትል ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ተገለፀ
አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 29 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) እየጣለ ያለው የበልግ ዝናብ በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋ ሊያስከትል ስለሚችል ከውዲሁ ጥንቃቄ እንዲደረግ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አሳሰበ።
በብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ በሚያዚያ ወር ትንበያ መሰረት በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በአማራ ክልሎች እንዲሁም መካከለኛውና ምዕራብ ትግራይ ክልል፣ የደቡብ ክልል መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ይኖራቸዋል።
በኦሮሚያ፣ ሶማሌ፣ ሲዳማ እና ደቡብ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች ከዝናቡ መጠን መጨመር ጋር ተያይዞ የጎርፍ አደጋ ሊያስከትል ይችላል ተብሏል።
በብሄራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ የአየር ትንበያ መሰረት በቀሪው የበልግ ወቅት ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች መለየታቸውን የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።
በዚህም መሰረት በኦሮሚያ ምዕራብ ሐረርጌ፣ ባሌ፣ አርሲ፣ ቦረና፣ ጉጂ እና ምዕራብ ጉጂ የጎርፍ ስጋት መኖሩን ተጠቁሟል።
በሶማሌ ክልል ሸበሌ፣ አፍዴር፣ ሊበን፣ ዶሎ፣ ፋፋን፣ ሲቲ፣ ዳዋ አንዳንድ አካባቢዎች ጎርፍ ሊኖር እንደሚችልም ተገምቷል።
በደቡብ ክልል ሀዲያ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ዳውሮ፣ ሰገን፣ ስልጤ፣ ጉራጌ አንዳንድ አካባቢዎችም የጎርፍ አደጋ ሊያጋጥም እንደሚችል ተገልጿል።
በሲዳማ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች እንዲሁም የድሬዳዋ ከተማና የገጠር ቀበሌዎችም የዝናቡን መጠን መጨመር ተከትሎ የጎርፍ ስጋት መኖሩን ኮሚሽኑ ጠቁሟል።
በመሆኑም ለጎርፍ ስጋት ተጋላጭ ለሆነው ማህበረሰብ የቅድመ ጥንቃቄና ወቅታዊ መረጃ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ ማሳሰቡን ኢዜአ ዘግቧል።
በብሔራዊ የጎርፍ ግብረኃይልና በክልሎች ግብረኃይል መካከል ተከታታይነት ያለው መረጃ ልውውጥ እንዲኖር የማድረግ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመላክቷል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!