Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ለጥምቀት በዓል የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለጥምቀት በዓል የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላለፉ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፦

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ።

ኢየሱስ ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ ከመጠመቁ በፊት የሰው ልጅ ውኃን የሚያውቀው በመዓትነቱና በዕንቅፋትነቱ ነበር። በኖኅ ዘመን የሰው ልጅ የጠፋው በውኃ ነው። እሥራኤላውያን ከግብጽ ወጥተው ወደ ከነዓን ሲጓዙ መንገድ የዘጋባቸው የኤርትራ ባሕር ነበር። ኢያሪኮን ተሻግረው ወደ ምድረ ርስት ሲገቡ የዘጋባቸው የዮርዳኖስ ወንዝ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በማዕከለ ዮርዳኖስ ሲቆም ግን ለመዓት የነበረው ውኃ ለበረከት ሆነ። ይሄው ዛሬም በየዓመቱ ወደ ውኃ ወርደን የጥምቀት በዓልን እናከብራለን።

በዓለም ላይ አዲስ ሀብት ይፈጠራል ብለን መጠበቅ የለብንም። ለችግር፣ ለመከራና ለመዓት ሲውሉ የነበሩ ነገሮችን ነው ወደ በረከት መቀየር ያለብን። የሰው ልጅ በጥንተ ጠላቱ ምክንያት በጥፋቱና በስንፍናው ውኃን የመዓት ማዝነቢያ አድርጎት ነበር። ክርስቶስ ያንኑ ውኃ ለበረከት እንዲሆን አድርጎ ለውጦታል።

በሀገራችን በጠላት ግፊት ለመዓት የዋሉና ለበረከት ልንቀይራቸው የሚገቡን ብዙ ሀብቶች አሉን። ለምሳሌ ብዙኅነታችንን ብንወስድ የመለያያና የመከፋፈያ ምክንያት እየሆነብን ነው። ካወቅንበት ግን ብዙኅነታችንን ለበረከት ማድረግ እንችላለን። ብዙኅነት ማለት ብዙ ዕሴት፣ ብዙ ጸጋ፣ ብዙ ሀብት፣ ብዙ ቅርስ፣ ብዙ ታሪክ፣ ብዙ ቋንቋ፣ ብዙ ባህል ማለት ነው። የሌላው ዓለም ሰዎች ይህን እኛ ያለንን ብዙ ሀብት ፍለጋ ዓለምን ይዞራሉ። እኛ ግን በሀገራችን ውስጥ ዓለምን የሚያስደንቅ ብዙኅነት አለን። አጠቃቀማችንን በጥበብ ብናደርገው ኢትዮጵያችን የሰው ልጅ ሀብቶች መናኸሪያ ናት።

ክርስቶስ ውኃን የቀደሰው ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ነው፤ ወደ ውኃው ሄዶ ነው፤ ማዕከለ ባሕር ቆሞ ነው። በውኃው ተጠምቆ ነው። እኛም መከተል ያለብን ይሄንን ነው። ራሳችንን ከሰቀልንበት ማውረድ፤ አንዳችን ወደ ሌላችን መሄድ፤ በሌላው መካከል መገኘት። ሌላውን የራሳችን ማድረግ፤ አንዳችን ከሌላችን መማር። በረከት የምናገኘው ዳር ቆመን አይደለም፤ መሐል ገብተን እንጂ። ከሩቅ ሆነን አይደለም፤ ወደዚያው ተጉዘን እንጂ። እላይ ነን ብለን አይደለም፤ ወደ ሕዝቡ ወረድ ብለን እንጂ።

ለመሆኑ ሰፈሮቻችን፣ ክልሎቻችን፣ የአስተዳደር ወሰኖቻችን የጉዳት ምክንያት እንዲሆኑ ለምን እንፈቅድላቸዋለን። ለምን የበረከት ምክንያት አናደርጋቸውም? ለምን የግጭትና የመለያየት መንሥኤ ይሆኑብናል? ለምን የእኔ የእኔ እንባባልባቸዋለን? ለምን የመጋደያ ዐውዶች እናደርጋቸዋለን? ኢትዮጵያ የሁላችን መሆኗን ብናምን፤ በወሰኖቻችንን ላይ ሰፋፊ ገበያዎችን ብንዘረጋ፤ አንዱን ክልል ከሌላው የሚያገናኙ አካባቢዎችን በጋራ ብናለማ፤ አንዳችን ወደ ሌላችን ሰፈር ሄደን አብረን የመኖር ነባር ዕሴታችን ብናጠናክር፤ የሁላችን የሆነውን ሜዳ ለጋራ እርሻ፣ ወንዙን ለጋራ መዋኛ፣ ተራራውን ለጋራ መዝናኛ፣ ጫካውን ለጋራ መናፈሻ ብናውለው መዓቱን በረከት አደረግነው ማለት ነው። የሚያጣላን ሀብቱ አይደለም፤ አስተሳሰባችን እንጂ። አዕምሯችን ውስጥ የገነባነውን ግድግዳ ካፈረስነው መሬት ላይ ያለው አጥር ገድቦ አይገድበንም። በአዕምሯችን ያስቀመጥነው ክልል ካልሆነ በቀር መሬት ላይ ያለው መንደር በፍቅር ከኖርንበት ጠብቦ አይጠበንም።

በታሪኮቻችንና በቅርሶቻችን፣ በጀግኖቻችንና በታሪካዊ ኩነቶቻችን ለምን እንጣላለን? እነዚህን ነገሮች የመዓት ማውረጃ ለምን እናደርጋቸዋለን? ለምን ወደ በረከት አንቀይራቸውም? ክፉውንም ደጉንም ታሪክ እንቀበለው፤ ያለፈውን በይቅርታ እንዝጋው፤ ታሪካዊ ቦታዎቻችንን የቱሪስት መስሕቦች እናድርጋቸው፤ ጀግኖቻችንን ለሚያከብሯቸው እንተውላቸው። የግድ ሁላችንም ካልተስማማንባቸው ብለን አንቆራቆስባቸው፤ ታሪካዊ ሁነቶችን አዳዲስ ዕሴቶች ጨምረን እንዘክራቸው፤ ያልተሟሉ ታሪኮቻችንን ጥናትና ምርምር አድርገን እናሟላቸው፤ እያፈረስን መሥራቱን ትተን እያሟላን እንሂድ፤ ያን ጊዜ ለመዓት እየዋሉ ያሉት ታሪካዊ ሀብቶቻችን የበረከት ምንጮች ይሆናሉ።

አደጉ የምንላቸው ሕዝቦች ሁሉ ያደጉት መዓቱን ወደ በረከት መቀየር በመቻላቸው ነው። የበለጸጉ ህዝቦች የብልጽግናቸው ምስጢር ሌላ ሳይሆን ችግርን ወደ እድል የመቀየር ችሎታቸው ነው፡፡ እነዚህ ህዝቦች በረዶውና ሙቀቱ ያስቸገራቸው፤ ረሐቡና ወረርሽኙ ያስመረራቸው፤ ጦርነትና ስደት ያሰቃያቸው ነበሩ። ችሎታቸውን በመጠቀም የሚያስመርረውን የአየር ንብረት፣ ፈታኙን መልከዐ-ምድርና አስቸጋሪውን ተፈጥሮ ወደ በረከት ቀይረው ዛሬ ምቹ ሀገር ገንብተዋል፡፡ ያለ ችግር መፍትሔ፣ ያለ ፈተና ጥንካሬ፣ ያለ ጨለማ ብርሃን አይኖርም፡፡ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ያሳደገው፣ ዘመናዊነትን ያመጣውና ሥልጣኔን የወለደው ችግርና ፈተና ነው። ሰዎች በብልሃት ከያዙት ከመዓት ውስጥ በረከት የሚሆን ነገር ማውጣት ይችላሉ።

“ሺ ጊዜ ጨለማን መውቀስ ብርሃንን አያመጣም” እንደሚባለው ባለንበት ተተክለን መዓቱን ብንረግምው በረከት አይሆንም። ከቁልሉ ላይ እንውረድ፤ ከከፍታው ዝቅ እንበል፤ ወደ ውኃው እንሂድ፤ በውኃው መካከልም እንቁም። ራሳችንን እላይ ሰቅለን ከተደላደልን የሚመጣ ለውጥ የለም። ሌላው ወደ እኛ እንዲመጣ ብቻ ከተመኘን የሚመጣ ለውጥ የለም። ውጡ ማለትን ትተን እኛ ራሳችን እንውረድ፤ ኑ ማለትን ትተን እንሂድ። ከዳር መሆንን ትተን መሐል እንግባ። ያን ጊዜ የምንፈልገው በረከት ይሆናል።

የሰው ልጅ ሊያየው ሲመኘው የኖረው ምሥጢር በጥምቀት የተገለጠው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ከላይ በመውረድ፣ ወደ ውኅውም በመሄድ፣ ውኅው ውስጥም በመግባት። ኤጲፋንያ – መገለጥ የተባለውም ለዚህ ነው። አብ በደመና፤ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል፣ ወልድ በዮርዳኖስ – አስደናቂው ምሥጢር የተገለጠው በዚህ ነው።

አንድ የምንሆንበት፣ የምንሠለጥንበት፣ የምንበለጽግበት፣ የምንዘምንበት፣ የምንፋቀርበት ምሥጢር እንዲገለጥልን፤ ኑ ሁላችንም ከላይ እንውረድ፤ የችግርና የፈተና ምንጭ በመሰለን ነገር መካከል እንገኝ። ከሩቅ መመልከታችን አቁመን መካከል ላይ እንቁም። በቋንቋው፣ በባህሉ፣ በበዓሉ፣ በታሪኩ፣ በወጉ መካከል እንሁን። በጥምቀት በዓል ሕዝቡ ሁሉ ቤቱን ትቶ፣ ሠፈሩን ትቶ፣ ጎጡን ትቶ ሁሉን ወደሚያካትተው ባሕር ይወርዳል። ሁሉን ወደሚያካትተው ሜዳ ይሰባሰባል። ኑ እኛም ምሽጎቻችንን ትተን ሁላችንም ወደምንገኛኝበት ወደ ሰፊው ሜዳ እንሂድ። የራሳችን የምለው ሁሉ ይዘን፤ ከሌላው ጋር አብረን ለመሆን ወደ ሰፊ ሜዳ እንሂድ።

በጥምቀት ጊዜ ሁሉም ያለውን ይዞ፣ በየወጉ ለብሶ፣ በየቋንቋው እየተናገረ፣ በየባህሉ እየጨፈረ በአንድ የጥምቀት ሜዳ ይገናኛል። ኢትዮጵያ ዓይነተ ብዙ፣ ጸጋ ብዙ፣ ሀብተ ብዙ፣ ባህለ ብዙ መሆንዋን ይመሰክራል። ሁሉም ይወርዳል፤ አንዱ በሌላው ሙዚቃ ይዋባል፤ አንዱ በሌላው ቋንቋ ያወጋል፤ አንዱ በሌላው ልብስ ያጌጣል፤ አንዱ የሌላውን ባህል ይወርሳል። ጠላታችን ለመዓት ሊያደርግብን የነበረውን ነገር ሕዝባችን ለምሕረት ያደርገዋል። የሚያዋጣንም ይኽ ነው።

መልካም የከተራና የጥምቀት በዓል ይሁንልን።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!

ፈጣሪ ሀገራችንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

አመሠግናለሁ!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.