Fana: At a Speed of Life!

የህዳሴ ግድብ የቴክኒክ ኮሚቴ የግድቡን የሙሌትና የሥራ ክንውን ሁኔታ ሪፖርት ለጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የቴክኒክ ኮሚቴ የግድቡን የሙሌት እና የሥራ ክንውን ሁኔታ ሪፖርት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ሪፖርት አቀረበ።

ኮሚቴው በተጨማሪም በግድቡ ዙሪያ ሲደረጉ በነበሩ የሶስትዮሽ የድርድር ሂደቶች ዙሪያ ማብራሪያ አቅርቧል።

ኮሚቴው በሪፖርቱ የአባይ ወንዝን ሀይድሮሎጂ፣ የግድቡን የሙሌት ጊዜያት፣ ለ”አስከፊ ድርቅ” እና ድርቅን ለመከላከል የሚሆን ቅድመ ዝግጅት እንዲሁም መረጃ በሚገባ ለመያዝና ለመለዋወጥ የተዘጋጁ የቅንጅት ስርዓቶች የመሳሰሉ ዐበይት ጉዳዮችን አካትቷል።

ከገለጻው በኋላ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ቀጣይ ክንውንን በተመለከተ አቅጣጫን ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ መካከል በህዳሴ ግድብ ላይ ሲካሄድ የነበረው ውይይት በጥሩ ውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል።

በውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የተመራው የህዳሴ ግድብ የቴክኒክ ኮሚቴ በእስካሁኑ የድርድር ሂደት እና የግድቡ ግንባታ ሂደት ዙሪያ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ሪፖርት አቅርቧል።

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ባቀረቡት ሪፖርትም፥ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሲደረጉ በነበሩ በድርድሮች የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቁ ስምምነቶች ላይ መደረሱን ጠቅሰዋል።

በድርድሮቹ ከዚህ ቀደም ለውይይቱ መጓተት እንደምክንያት ሲነሳ የነበረውን የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ከታችኛው ተፋሰስ አገራት ግድቦች የማያያዝ ውኔታ እንደቀር ማድረግ መቻሉንም አንስተዋል።

የግድቡን የግንባታ ሂደት አስመልክቶም፥ የግድቡ ግንባታ በአሁኑ ወቅት በተጠናከተረ ሆኔታ መቀጠሉን በመጥቀስ፤ በአሁኑ ወቅትም የግድቡ ግንባታ ከ70 በመቶ በላይ ማለፉን ገልፀዋል።

በያዝነው ዓመት መጨረሻ ግድቡን ውሃ መሙላት እንደሚጀመርም ነው የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በሪፖርታቸው ላይ የገለፁት።

ግድቡ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ በመንግስት በኩል ጠንካራ ክትትል እየተደረገ መሆኑንም በሪፖርታቸው አስታውቀዋል።

በአላዛር ታደለ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.