የሀገር ውስጥ ዜና

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓ ህብረት ምርጫውን የሚታዘቡ ባለሙያዎችን እንደሚልክ አስታወቀ

By Tibebu Kebede

May 11, 2021

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 3 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ከአሜሪካ እና ሩሲያ የተውጣጡ የባለሙያዎች ቡድን ስድስተኛውን ሃገራዊ ምርጫ ለመታዘብ እንደሚመጡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ፥ ምርጫውን ለመታዘብ ከህብረቱና ከሁለቱ ሃገራት የባለሙያዎች ቡድን እንደሚመጣ ገልጸዋል፡፡

በዚህም ከአውሮፓ ህብረት ስድስት አባላትን የያዘ ቡድን፣ ከአሜሪካ ሁለት ተቋማት የተውጣጣ እንዲሁም ከሩሲያና የአፍሪካ ህብረት ምርጫውን የሚታዘቡ ባለሙያዎች ይመጣሉ ብለዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የአውሮፓ ህብረት ቀድሞ ባስቀመጠው ቅድመ ሁኔታ ላይ የኢትዮጵያ አቋም እንዳልተቀየረም አስረድተዋል፡፡

ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው በአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ጀፍሪ ፊልትማን ከተለያዩ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ጋር ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን አንስተዋል፡፡

ልዩ መልዕክተኛው ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር በህዳሴ ግድብ ድርድር እና ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውንም አስታውቀዋል፡፡

በዚህ ወቅትም የድርድሩ ሂደት በሰላማዊ እና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲቋጭ አምባሳደሩ ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል ነው ያሉት።

በተያያዘም የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበርና የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ፌሌክስ ሲሼኬዲ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የሚካሄደውን ሰላማዊ ድርድር ማስቀጠል የሚያስችል ውይይት ያደርጋሉም ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ ቀደም ሲል በካይሮና ካርቱም ተመሳሳይ ውይይት ማድረጋቸውንም አስታውሰዋል።

በሌላ በኩል አምባሳደሩ በመግለጫቸው ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በኒጀር በነበራቸው ቆይታ፥ በሃገራዊ ምርጫ፣ በህዳሴ ግድብ ድርድር እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የተሳካ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡

በፍሬህይወት ሰፊው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!