ምርጫ 2013

እስካለፈው ረቡዕ ከ36 ሚሊየን በላይ መራጮች የድምፅ መስጫ ካርድ ወስደዋል

By Tibebu Kebede

May 15, 2021

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 7 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) እስካለፈው ረቡዕ ግንቦት 4 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ በተደረገ የመራጮች ምዝገባ ከ36 ሚሊየን በላይ መራጮች መመዝገባቸውን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ተናገሩ።

ቦርዱ በመራጮች ምዝገባ ሂደት እና ባጋጠሙ ችግሮች ዙሪያ ከፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር እየተወያየ ነው።

ይመዘገባል ተብሎ ተገምቶ ከነበረው መራጭ መካከል እስካለፈው ረቡዕ 78 ነጥብ 3 በመቶ ያህሉ መመዝገቡ በውይይቱ ላይ ተገልጿል።

በአጠቃላይ እስከ ረቡዕ ድረስ በነበረው የመራጮች ምዝገባም የሴቶች ተሳትፎ 46 በመቶ መሆኑንም ሰብሳቢዋ ገልጸዋል።

በምክክሩ በመራጮች ምዝገባ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮችና የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎችን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች የመራጮች መዝገባ ዘግይቶ መጀመርና፣ የምዝገባ ቁሳቁስ ለማጓጓዝ የትራንስፖርት እጥረት ችግሮች እንደነበሩ አንስተዋል።

ከክፍያ መዘግየት ጋር ተያይዞ የምርጫ አስፈጻሚዎች ጣቢያዎችን ዘግተው መጥፋት፣ መረጃ አለመስጠትና በተወሰኑ ጣቢያዎች ከመመሪያው ውጭ ከ1 ሺህ 500 በላይ ሰዎችን መዝግቦ መገኘትም ካጋጠሙ ችግሮች መካከል እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

ችግሮቹ በየደረጃው እንዲፈቱ የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደው የመራጮች ምዝገባው መከናወኑንም ተናግረዋል።

መራጮች በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ምዝገባ እንዲያካሂዱ ለማድረግ ከ150 ሺህ በላይ አጭር የሞባይል የጽሁፍ መልዕክቶች ተላልፈዋልም ነው ያሉት፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!