የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያና ኩባ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በትብብር የመስራት ፍላጎታቸውን ገለጹ

By Meseret Awoke

May 18, 2021

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ኩባ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በትብብር ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል፡፡

በኩባ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሽብሩ ማሞ ከኩባ የሳይንስ ቴክኖሎጂና የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ኤልባ ሮዛ ፔሬዝ ሞንቶያ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸው ወቅትም ሃገራቱ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተፈረሙ የመግባቢያ ስምምነቶችን መተግበር በሚቻልበት አግባብ ላይ መምከራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

ሃገራቱ በባዮቴክኖሎጂ፣ ሜትሮሎጂ እና ሥነ ፈለክ ጨምሮ በሳይንስና ቴክኖሎጂ በትብብር መስራት በሚቻልበት አግባብ ላይም መክረዋል፡፡

አምባሳደር ሽብሩ ስለመጪው ምርጫ፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ፣ ስለኢትዮ-ሱዳን የድንበር ውዝግብ እና በትግራይ ክልል እየተከናወነ ስላለው የሰብዓዊ ዕርዳታ እና የመልሶ ማቋቋም ስራዎች ለሚኒስትሯ ገለጻ አድርገውላቸዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!