ጠ/ሚ ዐቢይ የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ በከፊል ወደ ግል ለማዞር ከተቋቋመው አማካሪ ምክር ቤት አባላት ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 12 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሁለት የቴሌኮም አፕሬተሮች ፈቃድ ለመስጠት እየተሰራ ባለው ስራ ዙሪያ ከአማካሪ ምክር ቤት አባላት ጋር መከሩ።
ውይይቱ አዲስ የቴሌኮም ፈቃድ በመስጠት ሂደቱ ዙሪያ የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ በከፊል ወደ ግል ለማዞር ከተቋቋመው አማካሪ ምክር ቤት አባላት ጋር የተደረገ ነው።
በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ ኮሙዩኑኬሽን ባለስልጣን እንዳስታወቀው አዳዲስ የቴሌኮም ኦፕሬተሮችን ለማስገባት በወጣው ጨረታ ግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ የተባለ ጥምረት እና ኤም ቲ ኤን ኢንተርናሽናል መስፈርቶቹን አሟልተው አስገብተዋል ።
ግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ በውስጡ የእንግሊዙን ቮዳፎን፣ የደቡብ አፍሪካውን ቮዳኮም፣ የኬንያውን ሳፋሪ ኮም እና የጃፓኑን ሱሚሞቶን የያዘ ነው።
ጨረታው ሚያዝያ 18 ቀን 2013 ዓ.ም መከፈቱ ይታወሳል ።
ሁለቱ ኩባንያዎች ጨረታው ላይ መስፈርቶችን አሟልተው በመመረጣቸው አሁን ላይ ለመንግሥት ለውሳኔ ቀርቧል ።
የዛሬው ምክክር አላማም መንግስት ውሳኔ ከማሳለፉ በፊት ከአማካሪ ምክር ቤቱ ምክረ ሀሳብ መቀበል ነው ተብሏል።
በአላዛር ታደለ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!