ቦርዱ ምርጫው ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚካሄድ አስታወቀ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 12 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ግንቦት 28 ቀን ሊካሄድ የነበረው ሀገራዊ ምርጫ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚካሄድ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሶሊያና ሽመልስ በምርጫው ሂደት ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም የምርጫ ሂደቱ በሁሉም የመራጮች ምዝገባ በተጠናቀቀባቸው ቦታዎች ብቻ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
ከመራጮች ምዝገባ ጋር አቤቱታ የተነሳባቸው እና ምዝገባውን ዘግይተው የጀመሩ እና ያላጠናቀቁ የምርጫ ክልሎች እና ጣቢያዎች ላይ ግን በዚሁ ቀን አይካሄድም ብለዋል።
ምዝገባው ከተቀመጠለት ቀን ዘግይቶ ለመካሄዱ ምክንያት ደግሞ ምርጫ ቦርድ ማከናወን ያለበትን ስራ ለማጠናቀቅ፥ ሎጅስቲክስ እና ቁሳቁስን ለማዳረስ ምርጫው በአንድ ቀን ማካሄድ እንዲችል ለማድረግ አስፈላጊ እና ተጨማሪ የምርጫ አስፈፃሚ ቁጥር ለመጨመር በማሰብ መሆኑንም አስረድተዋል።
እስካሁን ከ138 ሺህ 350 በላይ አስፈፃሚዎችን በማንሳት ከ106 ሺህ 345 በላይ የሰው ሃይል ለማካተት በመሰራት ላይ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ከዚህ ባለፈም የምርጫ አስፈፃሚዎች ከምርጫ እና ከውጤት ቆጠራ እንዲሁም ውጤትን ይፋ ከማድረግ ጋር ተያይዞ ስልጠና እንዲወስዱ ለማስቻል በማሰብ መራዘሙንም በመግለጫቸው አንስተዋል።
በይስማው አደራው
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!