የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባኤ የአሜሪካ መንግሥት ያወጣውን መግለጫ አወገዘ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 12 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባኤ የአሜሪካ መንግስት ያወጣው መግለጫ ኢፍትሐዊ እና ሀገራዊ ሉዓላዊነትን የሚጥስ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ጉባኤው በኢትዮጵያ ለአሜሪካ አምባሳደር ጊታ ፓሲ ደብዳቤ ጽፏል፡፡
በደብዳቤውም በትግራይ ክልል እየተደረገ ላለው ሰብአዊ ድጋፍ እና እየታየ ላለው የሰብአዊ መብት መቆርቆር ምስጋናውን አቅርቧል፡፡
መማክርቱ በደብዳቤው የህወሃት ቡድን ለበርካታ አመታት ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ሲያካሂድ መቆየቱን አስታውሷል፡፡
ይሁን እንጅ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የትግራይ ክልልን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ያወጡት መግለጫ የተሳሳተና አግባብነት የሌለው መሆኑን አውስቷል፡፡
የሚኒስትሩ መግለጫም የተመድ መርህ የሆኑትን በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት እና ሉዓላዊነት ያለመጣስን የሚቃረን እና ኢ – ፍትሐዊ ነው ብሏል።
ሚኒስትሩ ከሚመለከተው አካል የምርመራ ውጤት ይልቅ ለህወሃት ቡድን የሃሰት ውንጀላ እውቅና መስጠታቸው አሳዛኝ መሆኑንም ነው መማክርቱ በመግለጫው ያነሳው፡፡
ከዚህ ባለፈም መግለጫው በህወሃት የሃሰት መረጃ የተመረኮዘ እና መሬት ላይ ያለውን እውነታ የሚክድ መሆኑንም መማክርቱ አንስቷል፡፡
በተጨማሪም በአማራ ክልል ልዩ ኃይል ሃይል ላይ በአሜሪካ መንግስት እየቀረበ ያለው ውንጀላ አግባብነት የሌለውና መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ አይደለምም ነው ያለው።
ከዚህ ባለፈም የአሜሪካ መንግስት ከቦታና መሬት ጋር በተያያዘ ያወጣው መግለጫ የተሳሳተ መሆኑንም አመላክቷል፡፡
የአሜሪካ መግለጫ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና መቋጫ አልባ ግጭት እና ሰብአዊ ቀውስ የሚያስከትል በመሆኑ አቋሙን በድጋሚ እንዲፈትሽ ጥሪ አቅርቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!