Fana: At a Speed of Life!

አዲስ ገቢ ተማሪዎች እስከ ግንቦት 30 ቀን ወደተመደቡባቸው ዩኒቨርሲቲዎች እንዲገቡ ይደረጋል

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 13 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ ገቢ ተማሪዎች እስከ ግንቦት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ወደተመደቡባቸው ዩኒቨርሲቲዎች እንዲገቡ ይደረጋል ሲል የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤት አሟልተው የተገኙ ተማሪዎች በተመደቡባቸው ዩኒቨርሲቲዎች እስከ ግንቦት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ እንዲገቡ እንደሚደረግ የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ አስታውቀዋል።
የዘንድሮውን የመመዘኛ ፈተና ካለፉት ከ147 ሺህ በላይ ተማሪዎች መካከል ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ 206 ተማሪዎች በሚፈልጉት የትምህርት መስክ እና የትምህርት ተቋም እንዲመደቡ መደረጉንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ከምደባ ጋር ተያይዞ ቅሬታ ካቀረቡ 23 ሺህ በላይ ተማሪዎች መካከልም ከ1 ሺህ 800 በላይ የሚሆኑት ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቶ የምደባ ማስተካከያ መደረጉንም ሚኒስትሩ በመግለጫቸው አንስተዋል።
የትምህርት መስክ ምርጫን አስመልክቶ በተፈጥሮ እና ማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ የተፈጠሩ ስህተቶችን በማረም 386 ተማሪዎች በመረጡት ዘርፍ እንዲመደቡ ተደርጓልም ነው ያሉት።
ከፍተኛ የጤና እክል ያለባቸው፣ ተመሳሳይ ጾታ ያላቸው መንትያዎች፣ ነፍሰ ጡር እና ከሁለት አመት በታች ልጅ ያላቸው እናቶች፣ አካል ጉዳተኞች እና ከአርብቶ እና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች የመጡ ተማሪዎችን ቅሬታን በማየት በቂ ማስረጃ ላቀረቡት አዎንታዊ ምላሽ ተሰጥቷል።
በሌላ በኩል የትምህርት ተቋም ምርጫን በሚመለከት ርቀትን፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን መሰረት አድርገው የቀረቡ ጥያቄዎችን ውድቅ ማድረጉን ሚኒስትሩ መግለጻቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.