የጋምቢያ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ያህያ ጃሜህ ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ እስራት እንደሚጠብቃቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ጥር 12፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የጋምቢያ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ያህያ ጃሜህ ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ እስራት እንደሚጠብቃቸው የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣን ገለጹ፡፡
የቀድሞው የጋምቢያ ፕሬዝዳንት ያህያ ጃሜህ ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በቁጥጥር ስር እንደሚውሉ የሀገሪቱ ፍትህ ሚኒስትር ታምባዱ ተናግረዋል፡፡
የፍትህ ሚኒስትሩ ጃሚህ ወደ ጋምቢያ ከተመለሱ በጨካኝ አገዛዛቸው ክስ እንደሚመሰርቱባቸው ገልጸዋል፡፡
ጃሜህ በፈረንጆቹ 2017 ከስልጣናቸው ከተነሱ በኋላ በኢኳተሪያ ጊኒ በስደት የሚገኙ ሲሆን በቅርቡ ወደ ሀገራቸው የመመለስ ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡
ይህንን ተከትሎም የፕሬዚዳንቱ ደጋፊዎች ጃሜህን በቁጥጥር ስር ማዋል “ደም መፋሰስ”ን ያስከትላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
ለ22 ዓመታት ጋምቢያን የመሯት ያህያ ጃሜህ በግድያ ፣ ሰዎችን በማሰቃየት እና በሰብአዊ መብት ጥሰቶች ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡
ምንጭ፡-ቢቢሲ