Fana: At a Speed of Life!

በሐረሪ የጥምቀት በዓል በህብረተሰቡና በጸጥታ አካላት ተሳትፎ የከፋ ችግር ሳይደርስ ተከብሯል-ፖሊስ

አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የጥምቀት በዓል ላይ ተስተውሎ የነበረው የጸጥታ ችግር ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት በተደረገው ጥረት የከፋ ጉዳት ሳይደርስ መከበሩን የሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ረመዳን ኡመር እንደገለጹት፥ ከጥር 10 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ አንዳንድ የጥፋት ተልዕኮ ያነገቡ አካላት በዓሉን ለማወክ ያደረጉት ጥረት በፀጥታ አካላትና በህብረተሰቡ ቅንጅት የከፋ ጉዳት ሳይደርስ ለመቆጣጠር ተችሏል።

በተፈጠረው የፀጥታ ችግርም 15 የጸጥታ አካላትን ጨምሮ በ19 ሰዎች ላይ ቀላል የአካል ጉዳት እንዳጋጠመና በንብረት ላይም ከፍተኛ የሆነ ጉዳት እንደደረሰ ኮሚሽነሩ ገልፀዋል።

እስከ አሁን ድረስም በድርጊቱ የተሳተፉ 20 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል ነው ያሉት።

በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት በማጣራትና አስፈላጊው መረጃ በማሰባሰብ ተጠርጣሪዎቹ ለህግ እንደሚቀርቡም ተናግረዋል።

ለህብረተሰቡ ትዕግስትና ትብብር ምስጋናቸውን የገለፁት ኮሚሽነር ረመዳን፥ ይሄንኑ በማጠናከር ክልሉ የሚታወቅበትን የሰላም የአብሮነትና የመቻቻል እሴቶችን እንዲያስቀጥል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በዛሬው እለትም ህብረተሰቡ እንደ ወትሮው ሁሉ ታቦታት ወደየደብራቸው በሰላም እንዲሸኙ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።

ምንጭ፥ ኢዜአ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.