የሀገር ውስጥ ዜና

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በጎንደር የጥምቀት በአል አከባበር ላይ በደረሰው አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኙ

By Tibebu Kebede

January 21, 2020

አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በጎንደር የጥምቀት በአል አከባበር ላይ በደረሰው የርብራብ መደርመስ አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች እና ለተጎዱ ወገኖች መፅናናትን ተመኙ።

ፓትሪያርኩ በትናንትናው እለት በጎንደር ከተማ በጥምቀት በዓል አከባበር ላይ የደረሰውን የርብራብ መደርመስ አደጋ አስመልክተው በዛሬው እለት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በመግለጫቸው፥ የከተራ እና የጥምቀት በዓላት በበርካታ አካባቢዎች በሰላማዊ መንገድ መጠናቀቁን ጠቅሰዋል።

ሆኖም በአንዳንድ አካባቢዎች ግን ችግሮች እንደነበሩ የገለፁት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፥ በተለይም በጎንደር ከተማ ሰዎች እንዲቆሙበት የተሰራው ርብራብ ተደርምሶ አደጋ መድረሱን ሰምተናል ብለዋል።

በአደጋው ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ እንዲሁም ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን ምእመናን መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች ቤተሰቦች መጽናናትን እና አካላዊ ጉዳት ለደረሰባቸው ብርታትን ተመኝተዋል።