የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ በ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር የተገነቡ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተመረቁ

By Meseret Awoke

May 26, 2021

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር የተገነቡ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተመርቀዋል።

በ2013 ዓ.ም የከተማ አስተዳደሩ 1 ሺህ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በምረቃው ላይ ተናግረዋል።

በጥቅሉ በቀን 90 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ መስጠት የሚያስችሉ የከርሰ ምድር የጥልቅ ጉድጓድ የንፁህ ውሃ ፕሮጀክቶች የተመረቁ ሲሆን፥ ከእነዚህ መካከል የቱሎ ጉዶ ፕሮጀክት በቀን 68 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ መስጠት የሚችል ነው ተብሏል።

ፕሮጀክቱ አቃቂ ቃሊቲ፣ ቦሌ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ እና ቂርቆስ ክፍለ ከተሞች እንዲሁም ፕሮጀክቱ በተገነባበት አካባቢ ለሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት እንደሚሰጥ ኢቢሲ ዘግቧል።

ከዚህ ጎን ለጎን የከፋ የውሃ ችግር ባለባቸው በተለያዩ አካባቢዎች ከተገነቡ ጉድጓዶች መካከል በቀን 22 ሺህ ሜትር ኪዩብ መስጠት የሚችሉ የውሃ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት በቅተዋል።

ለፕሮጀክቶቹ ከ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገባቸው ተገልጿል።

ፕሮጀክቶቹ የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ውሃ የማምረት አቅምን ከ574 ሺህ ወደ 664 ሺህ ሜትር ኪዩብ ማሳደጋቸው ተነግሯል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!