Fana: At a Speed of Life!

ወይዘሮ ጽዮን ተክሉ ከዓለም የፍልሰተኞች ድርጅት የአፍሪካ ቀንድና ምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 20 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ጽዮን ተክሉ ከዓለም የፍልሰተኞች ድርጅት የአፍሪካ ቀንድና የምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ ዳይሬክተር ሞሐመድ አብዲከር ጋር ተወያዩ።

በውይይት ወቅት በተለያዩ ሃገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ዜጎችን በተመለከተ አስፈላጊው የመረጃ ማጠናቀር ስራዎች በማከናወን በተቀናጀና በተቀላጠፈ ሁኔታ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል እየተደረገ ስላለው ጥረት አስረድተዋል።

በተጨማሪም የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ከመነሻ ሃገራት ብቻ ሳይሆን በመዳረሻ ሃገራትም ያሉ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር የሚሳተፉ አካላት እጅ ያለበት መሆኑን ጠቁመው፥ በዚህ ረገድ የመዳረሻ ሃገራትም ችግሩን ለመፍታት የበኩላቸውን ማድረግ እዳለባቸው አመላክተዋል።

በተያያዘም የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መስመሮች ላይ ጥናት በማድረግ ከአባል ሃገራት ጋር በመተባበር ችግሩን ከምንጩ በመከላከል ላይ ያተኮሩ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ከሚደረግ ሥራ ጎን ለጎን ዜጎች ህጋዊ በሆነ መንገድ በውጭ ሃገራት ለሥራ የሚሰማሩባቸውን መንገዶች ለማመቻቸት ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሃገራት ጋር የሥራ ስምምነቶችን ለመፈራረም እየሰራች መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በሀገር ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመርዳት መንግሥት ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር ዜጎቹን ለመርዳት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

በትግራይ ክልልም ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ከሚቀርበው ድጋፍ ውስጥ መንግስት 70 ከመቶ የሚሆነውን እየሸፈን መሆኑን ጠቅሰው፥ አንዳንድ የፖለቲካ አጀንዳ ያነገቡ አካላት ግን ተጨባጭ ድጋፍ ከማድረግ ይልቅ የመንግስትን ጥረቶች የሚያንኳስሱ ሪፖርቶች ላይ የተጠመዱ መሆኑን አንስተዋል።

አያይዘውም የዓለም የፍልሰተኞች ድርጅት ገለልተኝነቱን ጠብቆ ተጨባጭና እውነታውን የሚገልጽ ሪፖርት እንደሚያወጣ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የዓለም የፍልሰተኞች ድርጅት የአፍሪካ ቀንድና የምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ ዳይሬክተር ሞሐመድ አብዲከር በበኩላቸው ድርጅታቸው እያደረገ ያለውን ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን ማጠናከር የሚችልበትን ሁኔታ ለማየት በመቐለ ጉብኝት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በምስራቅ አፍሪካ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እንቅስቃሴ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የበርካታ ሃገራት ዜጎች ሰለባ መሆናቸውን ገልፀው፥ ድርጅታቸው በተለያዩ የሶማሊያ አካባቢዎች በኩል ተሻግረው በየመን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ስደተኞችን በመለየት ፍላጎታቸውንና ሰብዓዊ ክብራቸውን ጠብቆ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ እንደሚያደርግ አብራርተዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.