Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያውያን እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መስካሪ ሆነው መቆም አለባቸው – የብልፅግና ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 20 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)ኢትዮጵያውያን እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መስካሪ ሆነው መቆም አለባቸው ሲል የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጥሪ አቀረበ።
የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አገራዊና ጂኦ ፖሊቲካዊ ጉዳች ላይ በመምከር መልዕክት አስተላልፏል።
ሙሉ መልእክቱ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ልጆች፣
የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ወዳጆች፣
ክቡራትና ክቡራን፣
ሀገራችን ኢትዮጵያ የምትገኝበት ጂኦ ፖለቲካዊ ከባቢ ዛሬም እንደ ትናንቱ የዓለም ዓይን ማረፊያ ሆኖ ይገኛል።
ከሜዲትራንያን ባሕር ቀጥሎ በዓለም ታሪክ ላይ በሚደረጉ የንግድና ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎች የሚጠቀሰው ቀይ ባሕር ነው።
በዚህ ቀጣና ላይ የበላይነት መያዝ በዓለም አቀፍ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ይታመናል።
እናም ብዙ ሀገራት ከሌላ የዓለም ዳርቻ መጥተው በቀይ ባሕር ዙሪያ የጦር መንደሮችን ከመመሥረት፣ ወደቦችን ከማልማት፣ የንግድ መሥመሮችን ከመዘርጋት ባለፈ፣ በቀጣናው ፖለቲካ ላይ እጃቸውን ከማስገባት ተቆጥበው አያውቁም።
ኢትዮጵያ ደግሞ ከቀይ ባሕር ጋር አብራ የተፈጠረችና የኖረች ሀገር ናት።
ከጥንት ጀምሮ በቀይ ባሕር ሲደረግ በነበረው ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ እና የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ጉልሕ ሚና ነበራት።
የእኛን ተሳትፎ ከሌሎቹ ሀገራት ለየት የሚያደርገው የፍላጎታችን ምንጩ ከቀይ ባሕር ጋር ካለን ቅርበት ጋር የተያያዘ መሆኑ ነው።
ብንፈልግ እንኳን ከቀይ ባሕር ፖለቲካ ልናመልጥ አንችልም።
እንደ መጥፎ ዕድል ሆኖ አንዳንድ አካላት ቀይ ባሕር ላይ ያላቸው ፍላጎት የሚሳካ የሚመስላቸው ሀገራችን ስትዳከም ነው።
ይኼ ደግሞ እንደ ሉዓላዊ ሀገር በፍጹም ተቀባይነት የለውም።
የሀገራችንን ጥቅም በኃይል ወይም በዲፕሎማሲ ተጽዕኖ የማጣት ምንም ዓይነት ፍላጎት እንደሌለን መታወቅ አለበት።
እኛ እንደ ሀገር ከቀይ ባሕር ጥቅም ለማግኘት ስናቅድ ከሁሉም ጎረቤቶቻችን ጋር በሰጥቶ መቀበል መርሕ ተስማምተን እንጂ፣ ከማናቸውም ጋር እሰጣገባ ውስጥ በመግባት አይደለም።
የጋራ ፍላጎቶቻችንን በጋራ ለማሳካት ተግባብተን፣ በሰላማዊ መንገድ እንደምንሠራ የዲፕሎማሲ ታሪካችን ምሳሌ መሆን ይችላል።
ሌላው ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር አካባቢ ካላት ጂኦ ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ባለፈ የዓባይ ዋና ምንጭ በመሆኗም የአፍሪካን ቀንድና የሰሜን ምሥራቅ አፍሪካን ሁኔታ የመወሰን ዐቅም አላት።
ከግሪክ ሥልጣኔ ዘመን ጀምሮ አውሮፓውያንና እስያውያን ኢትዮጵያን ለማግኘት ከተጉበት ምክንያቶች አንዱ የዓባይን ምንጭ ለማወቅና ለመቆጣጠር እንደሆነ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።
በእነዚህ በሁለቱ ጂኦ ፖለቲካዊ ምክንያቶች የተነሣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ፣ ብሎም በአፍሪካ አህጉር ደረጃ ጠንካራ እየሆነች ከመጣች ጥቅማቸው የሚነካ የሚመስላቸው አካላት ሥጋት ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ ግልጽ ነው።
ነገር ግን አንድ መታወቅ ያለበት ሐቅ፣ ድሮም ሆነ ዛሬ ኢትዮጵያ የሌሎች ጥቅም ላይ ምንም ዓይነት ሥጋት የመፍጠር ዓላማ የላትም።
በተመሳሳይ የሀገራችንን ጥቅም ላይ ሌሎች ተጽዕኖ እንዲፈጥሩብን አንሻም።
ለውጡን ተከትሎ በቀጣናው የተረጋጋ ሁኔታ እንዲፈጠርና በቀጣናው ያለን ግንኙነት እንዲጠናከር የሠራናቸው ሥራዎች አሉ።
ከኤርትራ ጋር ያለን ግንኙነት መታደሱና በአጠቃላይ በቀጣናው ላይ የፈጠርነው መልካም ግንኙነትና ትሥሥር ቀጣናውን ለሚታዘቡ ኃይሎች ደስ የሚያሰኛቸው ጉዳይ እንዳልሆነ እሙን ነው።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በቅርቡ ከሱዳን ጋር የገባችበት ሁኔታ ከነበረን መልካም የሆነ የረጅም ዘመናት ግንኙነት አኳያ ሲፈተሽ ፈጽሞ መፈጠር የሚገባው እንዳልሆነ ግልጽ ነው። አሁንም ቢሆን ለዘመናት የቆየ በጎ ግንኙነት ታሳቢ በማድረግ በድንበር አካባቢ የተፈጠረውን ችግር በሰላማዊ ሁኔታ ለመፍታት እንሠራለን።
ሱዳኖችም ከመስፋፋትና ከጠብ ጫሪነት ወጥተው ለሰላማዊ መፍትሔ እንደሚቆሙ ተስፋችን ነው።
የኢትዮጵያን ሥልጣኔ ማየት የማይሹ አካላት ዋናው ዓላማቸው ደካማ ኢትዮጵያን መፍጠር ነው።
ለዚህ ደግሞ ሦስት መንገዶችን ይጠቀማሉ።
ኢትዮጵያን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ከጎረቤቶቿ ጋር በጦርነት መማገድ፣ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ማዳከም እና ኢትዮጵያውያንን በአካባቢና በእምነት ማጋጨት ናቸው።
ከጥንት ዘመናት ጀምሮ ኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆጠሩ ጦርነቶችን ከባዕድ ወራሪዎች ጋር አድርጋለች።
የእነዚህ ጦርነቶች ዋና ዓላማ ሀገሪቱ ፋታ አግኝታ የሥልጣኔ መንገዶቿን እንዳትከተል ማድረግ ነው።
በእርግጥም ጦርነቶቹ በተወሰነ አዳክመውን አልፈዋል።
ከጦርነቱ ባሻገር የኢትዮጵያን የንግድ መሥመሮች በመያዝ፣ ከባሕር በር ውጭ በማድረግ እና ዓለም አቀፍ ብድርና ርዳታ አግኝታ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን እንዳታካሂድ ዕንቅፋት በመፍጠር የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማሰናከል ጥረት ተደርጓል።
የዓባይ ግድብንም ሆነ ሌሎች ግድቦችን ለመገንባት ኢትዮጵያ በታሪኳ ያደረገቻቸው ጥረቶች ያልተሳኩበት አንዱ ምክንያት ይኼ ነበር።
ከዓባይ ወንዝ ተገቢውን ጥቅም ማግኘት እንዳንችል ካደረጉን ምክንያቶች መካከል ለፕሮጀክቶቹ ማስፈጸሚያ የሚውል ገንዘብ እጥረት፣ የእርስ በርስ ጦርነት እና የዓለም ፖለቲካ ተለዋዋጭ አሠላለፍ የሚጠቀሱ ናቸው።
አንድ አንድ ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ በጎረቤት ሀገራት የሚቃጡ ጦርነቶችን በመቆስቆስና በመደገፍ፣ በሀገር ውስጥ የፖለቲካ ዐማጽያንን በመደገፍና የእርስ በርስ ጦርነትን በማቀጣጠል፣ ለጋሽ ሀገራት የገንዘብ ድጋፍ እንዳያደርጉ በመጎትጎት፣ ወዘተ. ዓባይን እንዳንጠቀም የሚቻላቸውን ሁሉ ሲያደርጉ እንደ ነበረ ይታወቃል።
በኢትዮጵያ ላይ ሁለንተናዊ ጫና ለመፍጠር በሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽነት ስም እንዲሁም በሰላምና በሰብአዊ መብት ስም ተጽዕኖ ሲደረግ ይታያል።
ለውጡን ተከትሎ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ስናደርግና የፖሊሲ ነጻነታችንን ለማስጠበቅ ስንንቀሳቀስም እግራችንን ከሚጎትተን አንዱ፣ በዲፕሎማሲ መልኩ የሚመጣ ጫና ነው።
እኛ በአሸባሪነት ለመፈረጅ የተገደድንበትን የጁንታ የጥፋት እንቅስቃሴ የዲፕሎማሲ አጋሮቻችን በቀላሉ ተመልክተው ጫና ሲያደርጉብን ይታያል።
የመጨረሻው ምጥ ልጁ የሚወለድበት ነው።
ዓባይን በራሳችን ገንዘብ ገንብተን ወደ ፍጻሜው ማድረሳችን፣ በቀይ ባሕር የነበረንን ተጽዕኖ ፈጣሪነት ለመመለስ ተግተን መሥራታችን፤ ከኤርትራ ጋር የነበረንን የተበላሸ ግንኙነት አድሰን ቤተሰባዊነትን መመሥረታችን፤ የጁንታውን ጦርነት እነሱ ባልጠበቁት መንገድ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአሸናፊነት መወጣታችን፤ የራሳችንን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የዐሥር ዓመት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መንደፋችን፤ የሕዝቦችን አንድነትና ትብብር በማቀንቀን ወደ ጠንካራ ሀገርነት መጓዛችን ያላስደሰታቸው ኃይሎች እንዳሉ ግልጽ ሆኗል።
ይኽ ወቅት ኢትዮጵያውያን ሁለት ነገሮችን ለይተው በጽናት የሚቆሙበት ጊዜ ነው።
የውስጥ ጉዳያችንንና የውጭ ጉዳያችንን።
የውስጥ ጉዳዮቻችንን በክርክር፣ በልሂቃን ድርድር እና በውይይት የምንፈታቸው ናቸው።
የተፈጠሩት በአንድ ሌሊት አይደለም።
የሚፈቱትም በአንድ ሌሊት አይሆንም።
እኛ የዘመናት ችግር ወራሾች ነን።
ዕዳ ያለበት ሰው ሁለት ነገር እንዲሠራ ይገደዳል።
በአንድ በኩል ያልነበረበትን ዘመን ዕዳ ይከፍላል፤ በሌላ በኩል ደግሞ አሁን በዘመኑ የገጠሙትን ችግሮች ይፈታል። እኛም የገጠመን ይኼ ነው።
የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር የውስጥ ችግሮቻችንን መፍታታችን አጠራጣሪ አይደለም።
የውጭው ፈተና ግን ጊዜ የሚሰጠን አይደለም።
የመርከቧ ተሳፋሪዎች መከራከርና መፎካከር የሚችሉት መጀመሪያ መርከቧ ካለች ብቻ ነው።
እየሰጠሙ መብትም፣ ውይይትም፣ ክርክርም፣ ድርድርም፣ ትብብርም፣ ፉክክርም የለም።
የሀገርም ጉዳይ እንዲሁ ነው።
አባቶቻችን የሀገራችንን ነጻነትና ሉዓላዊነት አስከብረው የኖሩት የሀገራቸው የውስጥ ችግሮች ሳይፈትኗቸው ቀርቶ አይደለም።
በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ውስጥ የገጠሙንን ግጭቶች፣ የዜጎች ሞትና መፈናቀል እንዲፈጠር እያደረጉ ያሉ ኃይሎች ለሀገራችን ሰላምም ሆነ ለዜጎቻችን ህልውና ሥጋት በማይሆንበት ደረጃ በቁጥጥር ሥር የማዋልና የሕግ የበላይነትን የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ዛሬም ከግራና ከቀኝ የተቃጣብንን አደጋ ለመቀልበስ፤ ቀልብሰንም ወደጀመርነው የሥልጣኔ ጉዞ ለመገሥገሥ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ፣ እንደ አንድ ልብ መካሪ ሆነን የምንቆምበት ወቅት ነው።
በተለይም ከፊታችን ያሉብን ሁለት ሀገራዊ ተልዕኮዎች በሚገባ በመወጣት ኢትዮጵያ – ልጆች እንዳሏት ማረጋገጥ አለብን። ሁለቱ ሀገራዊ ተልዕኮዎች የሕዳሴውን ግድብ ሁለተኛ ሙሌት ማከናወንና ሀገራዊውን ምርጫ በስኬት ማጠናቀቅ ናቸው።
ሁለቱም የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያንን የነገ ዕጣ ፈንታ ይወስናሉ።
ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ ለመጠናቀቅ የመጨረሻው ምእራፍ ላይ ደርሰናል።
የተወዳዳሪዎችና የመራጮች ምዝገባ ተከናውኖ፣ ምርጫ ቅስቃሳና ሌሎች ለምርጫው የሚያስፈልጉ ተግባራት ተፈጽመው ከሞላ ጎደል አሁን የቀረው የድምፅ አሰጣጥ ሒደት ነው።
ይኽንን በስኬት ማጠናቀቅ ለሀገራችን ትልቅ ድል ይዞ ይመጣል።
ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የምታደርገውን ሽግግር አንድ ደረጃ እንደሚያሳድገው ምንም ጥርጥር የለውም።
በዚህ አጋጣሚ ምርጫው ዴሞክራሲያዊና ተአማኒነቱን ጠብቆ እንዲፈጸም ሁሉም አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ያላሰለሰ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
በመንግሥት በኩል የተጀመሩ የሕግ የበላይነትና ሰላምን የማስከበር ሥራዎችን አጠናክሮ ይቀጥላል።
በተለያዩ አጋጣሚዎች የተፈናቀሉ ዜጎቻችንንም በፍጥነት ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ የተለያዩ አካላትና ሕዝባችንን በማስተባበር ይሠራል።
መንግሥት በትግራይ ክልል የጀመረውን የመልሶ ግንባታ ሥራ እና የሰብአዊ ድጋፍ ከአጋሮች ጋር አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።
የእምነትና የብሔር ልዩነቶቻችንን እንደ ጸጋ ብቻ በመቁጠር፤ አንድ ሆነን እንደ ብዙ፤ ብዙ ሆነን እንደ አንድ በመንቀሳቀስ፤ የጀመርናቸው ፕሮጀክቶች ሁሉ በተገቢው ደረጃና ፍጥነት በማጠናቀቅ፤ ከቃል ይልቅ ለተግባር ቅድሚያ በመስጠት፤ የመከላከያ ኃይላችንን በሙሉ ዐቅም በመደገፍ፤ የፖለቲካ አመራራችንን በሀገራዊው ተልዕኮ ላይ እንዲያተኩር በማድረግ፤ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ዲፕሎማቶቻችን ሀገራችንን በዓለም መድረክ በብቃት መወከላቸውን በማስከበር – ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ኢትዮጵያን መውደዳቸውን በአመቺ መንገዶች ሁሉ እየገለጹ፣ ከኢትዮጵያና ከሕዝባቸው ጎን መሆናቸው በማሳየት – በኢትዮጵያዊነት ስሜት አንድ ሆነው እንዲቆሙ ጥሪ እናደርጋለን።
በዚህ አጋጣሚ ከሕዳሴ ግድባችን ጋር በተገናኘ ኢትዮጵያ ማግኘት ያለባት ጥቅም እንዲጠበቅ አንደበት ሆናችሁ የሀገራችን ድምፅ እንዲሰማ፣ ለሐቋ ስትሉ በዓለም አቀፍ መድረኮችና በመካከለኛው ምሥራቅ ሚዲያዎች ላይ እየሞገታችሁ ያላችሁ ብርቅዬዎች ኢትዮጵያ ለእናንተ ትልቅ ክብር አላት።
የሀገር ልጅነታችሁን ከስም ባለፈ በተግባር አስመስክራችኋል። ከሀገራዊ ሉአላዊነታችን ጋር በተገናኘም የሚገጥሙንን ተጽዕኖች በሙያችሁና በድምፃችሁ እየመከታችሁ ያላችሁ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች፣ እናት ሀገራችን በጦር ሜዳ ላይ ጀብዱ ከፈጸሙላት ጀግኖቿ ለይታ አታያችሁም።
ታሪክም ሲዘክራችሁ እንደሚኖር ጥርጥር የለውም።
የብልጽግና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ
ግንቦት 20፣ 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.