ኢትዮጵያውያን የውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነትን በመቃወም በጣሊያን ሮም ሰልፍ አካሄዱ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የመንግስትን አቋም በመደገፍ የውጭ ሃይሎች በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉ ያለውን ጣልቃ ገብነትና ጫና በመቃወም ሰልፍ አካሂደዋል።
ሰልፈኞቹ በዚህ ጊዜ የግብፅና ሱዳንን የሴራ አካሄድ የተቃወሙ ሲሆን የኢትዮጵያን ህዝብናመንግስት አቋም በመደገፍ በጣሊያን ሮም ከተማ ሰልፍ አደርገዋል።
ሰልፈኞቹ አሜሪካ በኢትዮጵያና በኤርትራ ብሎም በአፍሪካ ቀንድ ላይ ያላትን ያልተገባ ጣልቃ ገብነት፣የሱዳንን የደንበር ወረራ እና በህዳሴ ግድብ ድርድር ላይ ሱዳን እና ግብፅ እየሄዱበት ያለውን ሴራ አውግዘዋል።
እንዲሁም የምዕራባዉያን ሚዲያዎችን ከኢዲቶሪያል ፖሊሲ ያፈነገጠ ዘገባ ተቃውመዋል።
እንዲሁም አሁን ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ከምዕራባውያን ጫና ሳይሆን ለተፈናቀሉ እና በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች እገዛ የሚፈልጉበት ወቅት መሆኑን በአፅንዖት ገልፀዋል።
በተጨማሪም የግድቡ ሁለተኛ ሙሌት በተያዘለት እቅድ መሰረት እንዲካሄድና ቀጣዩ ምርጫ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት እንደሚደግፉ ገልፀዋል።
የህዋሃት የጥፋት ቡድን አሁንም ከአንዳንድ የውጭ የጥፋት ሽሪኮቹ ጋር በመሆን የተካነበትን የሃሰት ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ጫና ለመፍጠር የሚችለውን እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሰልፈኞቹ እየደረሰ ያለውን ጫና ለመቀነስ፣ሰብዓዊ እገዛ ለማድረግ እና አገራዊ ፕሮጀክቶችን ለማስቀጠል እንዲሁም የአገሪቱን አንድነት ለማስጠበቅ ሁሉም በያሉበት ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ጎን እንደሚቆሙ ተናግረዋል።
ከሰልፉ ጎን ለጎን ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ አስር ሺህ ዩሮ ለግድቡ የቦንድ ግዢ በመግዛት አጋርነታቸውን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!