Fana: At a Speed of Life!

የውጭ ጫናዎችን ለመቋቋም ዳያስፖራው ገንዘቡን በህጋዊ መንገድ በመላክ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ውሳኔ ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ጫናዎችን መቋቋም እንዲቻል ዳያስፖራው ገንዘቡን በህጋዊ መንገድ በመላክ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለጸ።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ውሳኔን ተከትሎ በኢትዮጵያ ላይ እየተሰነዘሩ ያሉ ጫናዎችን መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የኢፌዴሪ ሚሲዮኖችና ልዩ ልዩ የዳያስፖራ አደረጃጀቶች የተሳተፉበት በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲና በካናዳ የኢፌዴሪ ኤምባሲ ቅንጅት የተዘጋጀ የበይነ መረብ ውይይት ተካሂዷል፡፡

መድረኩን በንግግር የከፈቱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ባስተላለፉት መልዕክት፥ ዳያስፖራው እያከናወነ ያለው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ተግባር አበረታች መሆኑን አንስተዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ጥቅም በተጻራሪ የቆሙ ሃይላት የሚያራምዱትን የተደራጀና የተቀናጀ ጫና ለመቋቋም ከመንግስትም ሆነ ከዳያስፖራው ብዙ መስራት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም እነዚህ ሃይላት ውስጣዊ ተጋላጭነታችንን መንጠላጠያ፣ በማደግና በመልማት ጉዟችን ላይ እንቅፋት በማበጀት ደካማ ሃገር ሆነን እንድንቀር ስትራቴጂ ነድፈውና ተቀናጅተው እየሰሩ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡

የዕለቱ ተጋባዥ እንግዳና የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ በበኩላቸው፥ መንግስት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ውሳኔን ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን ችግር ማቃለል እንዲቻል ልዩ ልዩ ስልቶችን ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከነዚህም መካከል የውጪ ንግድን ለማስፋፋትና ከዳያስፖራው የሚላከውን የውጭ ምንዛሪ መጠን ለማሳደግ የፖሊሲ አማራጮችን ማየት እንደሚገኝበት አብራርተዋል፡፡

አያይዘውም ጫናውን መቋቋምና ይህን ከባድ ጊዜ በጋራ ማለፍ እንዲቻል ዳያስፖራው ገንዘቡን በህጋዊ የመላኪያ መንገዶች ብቻ ተጠቅሞ እንዲልክ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት በበኩላቸው፥ ዳያስፖራው ለሃገራዊ ፕሮጀክቶችና ወቅታዊ ጥሪዎች እያደረገ ስላለው ድጋፍ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡

ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ውሳኔ ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ጫናዎችን መቋቋም እንዲቻልም ዳያስፖራው ገንዘቡን በህጋዊ መንገድ በመላክ፣ መጠኑን በመጨመርና የተጠናከረ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራ በማከናወን ሃገራዊ አለኝታነቱን በድጋሚ ሊያረጋግጥ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በመድረኩ የተሳተፉ የኢፌዴሪ አምባሳደሮች አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ፣ አምባሳደር ፍጹም አረጋ፣ አምባሳደር ሂሩት ዘመነ እንዲሁም አምባሳደር ዘነበ ከበደ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ውሳኔ ሊያስከትላቸው ስለሚችላቸው ጫናዎች፣ ጫናዎቹን ለመቋቋም በየተመደቡባቸው ሃገራት እያከናወኗቸው ስላሉት ተግባራት እንዲሁም በሃገር ቤትና በዳያስፖራው መካከል ቅንጅት በመፍጠር መሰራት ስላለባቸው ስራዎች ዝርዝር ሃሳቦችን አቅርበዋል፡፡

የዳያስፖራ አደረጃጀት ተወካዮችም በበኩላቸው፥ ባከናወኗቸው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራዎች ውጤቶች ቢመዘገቡም በቂ አለመሆናቸውን፣ የተናበበና የተቀናጀ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚያስፈልግ፣ በተለይም ኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን ካላቸው ቁጥር አንጻር በአሜሪካ ምክር ቤቶች ተመራጮች ላይ ተጽዕኗቸውን ለማሳደግ መስራት እንዳለባቸው ተጠቅሷል፡፡

እንዲሁም በመንግስት በኩል መረጃዎችን በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ፣ የህዝብ ግንኙነትና የኮሙዩኒኬሽን ስራዎችን ለማጠናከር ብሎም በዘርፉ አቅም ያላቸው ተቋማትን በመቅጠር የሃይል ሚዛኑን ለማስተካከል ሊሰራ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

በመጨሻም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ በመልዕክታቸው፥ መድረኩ ገንቢና ጠቃሚ ሃሳቦች የተንሸራሸሩበት እንደነበር አንስተው፤ የተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶችን በዕቅድ ውስጥ በማከተት ለመመለስ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

በተጨማሪም ዋናው ችግራችን ውስጣዊ መሆኑን ተረድተን ከዚህ አንጻር ሁላችንም ያለንን አቅም አሟጠን በመስራት ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት መንቀሳቀስ ይጠበቃል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.