የውጭ ሃገራትን ጣልቃ ገብነት በመቃወም ሃገራዊ አንድነትን ማስጠበቅ ያስፈልጋል – ሲኖዶሱ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ከግንቦት 17 እስከ ግንቦት 20 ቀን 2013 ዓ.ም ሲያካሂድ የቆየውን ጉባኤ አጠናቀቀ።
ከቤተክርስቲያን ሰላም እስከ ሃገር ደህንነት፣ ከቀያቸው ስለተፈናቀሉና ለስደት ስለተዳረጉ፣ በተለያዩ ቦታዎች ስለሚታዩ አለመግባባቶች እና ሌሎች ማህበራዊና መንፈሳዊ ጉዳዮች ላይም ውሳኔዎችን አሳልፏል።
በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት የጠፋ የሰው ህይወትና ንብረት በየአህጉረ ስብከቱ ተጣርቶ እንዲቀርብ ወስኗል።
የአምልኮ ስፍራ፣ ስም እና ተጠብቆ የቆየ የቤተክርስቲያኗ ክብር እንዲሁም በካህናትና ምእመናን ላይ እየደረሰ ያለ ሞትና ስደት ከየአህጉረ ስብከቱ እንዲጣራና መንግስትም አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግ አሳስቧል።
የአምልኮ ስፍራዎች በተለይም በዩኔስኮ የተመዘገቡ ስፍራዎችን ልዩ ጥበቃና ትኩረት በመስጠትም ከእነማንነታቸው ተጠብቀው እንዲቆዩ መንግስት የበኩሉን እንዲወጣም ጠይቋል።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ዳር ድንበሯንና አንድነቷን አስጠብቃ የኖረች ሃገር መሆኗን የጠቀሰው ቅዱስ ሲኖዶሱ፥ አሁን የሚታየው የውጭ ሃገራት በሃገሪቱ ህልውና ላይ እያደረጉት ያለውን ጣልቃ ገብነት በመቃወም ሃገራዊ አንድነቱን ከምንጊዜውም በላይ ማስጠበቅ ያስፈልጋልም ነው ያለው።
የህዳሴ ግድብ ከድህነት ለመውጣት አንድ እርምጃ ወደፊት መሆኑን የጠቀሰው ጉባኤው የአንድነት ማሳያ የሆነውን ይህንኑ ግድብ ፍጻሜውን በማፋጠን ከጨለማ ለመውጣት መላው ኢትዮጵያውያን እንዲረባረቡ ጥሪ አቅርቧል።
በአረንጓዴ አሻራ በኩልም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ልምላሜን ስታስፋፋ መኖሯን በማስታወስ መንግስት ባዘጋጀው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በመሳተፍ መላው ዜጋ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ነው ጥሪውን ያቀረበው፡፡
በሌላ በኩል ህብረተሰቡ ራሱን ከኮቪድ19 ወረርሽኝ በመጠበቅና በተለይም ባለመግባባት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በተለመደው የኢትዮጵያዊነት መተሳሰብ እንዲደርስላቸውም ጥሪ ያአቅርቦ ቀጣዩ ሃገራዊ ምርጫም ጨዋነት የሚመሰከርበት ምርጫ እንዲሆን የሰላም ጥሪውን አስተላልፏል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ከሰኔ 14 ቀን ጀምሮ እስከ ሃምሌ 4 ቀን 2013 አ.ም. ድረስ በመላው ሃገሪቱና በውጭ ባለችው ቤተ ክርስቲያን ጸሎተ ምህላ እንዲደረግ ውሳኔ በማሳለፍም አመታዊ ስብሰባውን አጠናቋል።
በማህሌት ተክለብርሃን
ፎቶ፡-ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙሃን አገልግሎት
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!