Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ ነገ በሰው የመነገድና ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቀረበ ረቂቅ አዋጅን ያፀድቃል

አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ስብሰባውን ጥር 14 ቀን 2012 ዓ.ም ያካሂዳል።
በስብሰባውም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል።
 
በዚህም የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሰው የመነገድ እና ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቀረበ ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ያቀረቡትን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ አዋጁን ያጸድቃል ተብሎ ነው የሚጠበቀው።
 
እንዲሁም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የ2012 በጀት ዓመት የ6 ወር እቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን የሚያዳምጥ ይሆናል።
 
በሰው የመነገድ፣ ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና በህገ-ወጥ መንገድ ለስራ ወደ ውጭ ሀገር መላክ ወንጀሎች በዜጎች አካል፣ ህይወት እና ደህንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ እና ለሰብዓዊ መብት ጥሰት እያጋለጡ በመሆናቸው ረቂቁ መዘጋጀቱ ተነግሯል፡፡
 
እንዲሁም በሰው የመነገድ በተለይም በሴቶችና ሕጻናት መነገድን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና ወንጀል ፈጻሚዎችን ለመቅጣት እና ሰውን በህገ-ወጥ መንገድ በየብስ፣ በባህርና በአየር ማስወጣትና ማስገባት መከላከል የሚያስችሉ አሰራሮችን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በማውጣቱና ኢትዮጵያም ስምምነቱን ያጸደቀች በመሆኑ ይህ ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱ ነው የተነገረው፡፡
 
ከዚህ ባላፈም ወንጀሉን ለመከላከል፣ ወንጀል ፈጻሚዎችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ፣ የተጎጂዎች ጥበቃና መልሶ ለማቋቋም በተለይም ለወንጀሎቹ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰቡ ክፍሎችን ተደራሽ የሚያደርግና የተጎጂዎችን ዕድሜ፣ ጾታና ልዩ ፍላጎት ያማከል ተግባር መፈጸም እና ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማጠናከር የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ ማውጣት እና ስርዓት መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑም ነው ተብሏል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.