Fana: At a Speed of Life!

ሊባኖስ አዲስ መንግስት መመስረቷን ይፋ አደረገች

አዲስ አበባ፣ጥር 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ ) ለወራት በተቃውሞ ስትናጥ የቆየችው ሊባኖስ አዲስ መንግስት መመስረቷን አስታውቃለች።

አዲሱ መንግስት ሂዝቦላህ እና አጋሮቹ አዲስ ካቢኔ ለማዋቀር በቀረበው ሃሳብ ላይ መስማማታቸውን ተከትሎ የተመሰረተ ነው ተብሏል።

ይህም በሙስና እና በመልካም አስተዳደር እጦት በተቀሰቀሰው ህዝባዊ አመጽ የተጎዳውን የሀገሪቱ ኢኮኖሚ መታደግ ያስችላል ነው የተባለው።

የሃገሬው ዜጎች በፍጥነት ምርጫ እንዲካሄድ እና በገለልተኛ ተራማጅ አካል የሚመራ ካቢኔ እንዲቋቋም እየጠየቁ ነው።

20 አባላት ያሉት አዲሱ ካቢኔ በቤሩት የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር በሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ሀሰን ዲያብ የሚመራ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔያቸውን ህጎችን እና ደንቦችን መሰረት አድርገው ማዋቀራቸውን ተናግረዋል።

መንግስታቸው የህዝቡን ፍላጎት ለማርካት ገለልተኛ የፍትህ አካላት፣ ህገ-ወጥ አሰራሮችንና የተጎዳውን ኢኮኖሚ ለመጠገን ይሰራልም ነው ያሉት።

ከዚህ ባለፈም ካቢኔው ተጠያቂነት ያለበትና ከመንግስት አካላት መካከል አንዳቸውም ለቀጣዩ ምርጫ እንደማይሳተፉ ጠቁመዋል፡፡

በሊባኖስ በሙስና እና በመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት በተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ሰዓድ ሀሪሪ ስልጣን መልቀቃቸው ይታወሳል።

ምንጭ፡-አልጀዚራ

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.