Fana: At a Speed of Life!

የመገጭ ግድብ የመጠጥ ውሃና መስኖ ፕሮጀክትን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 25 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር የመገጭ ግድብ የመጠጥ ውሃና መስኖ ፕሮጀክትን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ተናገሩ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ የፕሮጀክቱን የግንባታ ሂደት በስፍራው ተገኝተው ጎብኝተዋል፡፡

ግንባታው ከተጀመረ ስምንት ዓመታት ያስቆጠረው ይህ ፕሮጀክት ከፍተኛ መዘግየት የታየበት መሆኑን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ የክልሉ እና የፌደራል የስራ ሀላፊዎች ባስቀመጡት አቅጣጫ በስድስት ወራት ውስጥ የፕሮጀክቱ አፈፃፀም ተስፋ ሰጪ መሆኑን ተናግረዋል።

በፕሮጀክቱ ደካማ አፈጻጸም ያሳዩ ተቋራጮች ውል ተቋርጦ 10 አዲስ ተቋራጮች ወደ ስራ መግባታቸውንም ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም አሁን ላይ በፕሮጀክቱ ለውጥ እየታየ ነው ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።

45ሺህ አባወራዎችን የመስኖ ተጠቃሚ የሚያደርገው እና የጎንደር ከተማን የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር በዘላቂነት ይፈታል የተባለው ይህን ፕሮጀክት በቀጣይ ዓመት ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተቋራጮች በኩል የቀረቡ የግብዓት ችግሮችና የሶስተኛ ወገን ችግሮች በፍጥነት እንዲፈቱ ርዕሰ መስተዳድሩ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

የፕሮጀክቱ አፈፃፀም 72 በመቶ የደረሰ ሲሆን የተመደበለት በጀትም 5 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር መድረሱ ተነግሯል ።

በምናለ አየነው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.