የሀገር ውስጥ ዜና

የወላይታ ሶዶ ከተማ የመርካቶ የገበያ ማዕከልን መልሶ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ

By Meseret Awoke

June 02, 2021

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳ ከዚህ ቀደም በእሳት አደጋ የወደመውን የወላይታ ሶዶ ከተማ የመርካቶ የገበያ ማዕከልን መልሶ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፥ ከጥቂት ወራት በፊት በመርካቶ ገበያ ማዕከል በደረሰው ጉዳት በርካቶች የእለት ጉርሳቸውን አጥተዋል።

የደረሰውን ጉዳት በደስታ ለመለወጥ የማዕከሉ መገንባት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፥ ለተቸገሩ ወገኖች ፈጥነው ለደረሱ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል ።

የሶዶ ከተማ ከንቲባ አቶ መርክኔ ማለዳ የገበያ ማዕከሉን መልሶ ለመገንባት በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ እንደገለጹት፥ ዘመናዊ የሶዶ ከተማ የገበያ ማዕከል ፕሮጀክት አጠቃላይ ወጪ ወደ ግማሽ ቢሊየን ብር ይጠጋል ብለዋል።

በፕሮግራሙ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳን ጨምሮ፥ የደቡብ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ፣ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ተሾመ ቶጋ፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ እና ሌሎች የደቡብ ክልል ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በወላይታ ዞን ጠበላ ከተማ አስተዳደር የጠበላ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልን መርቀው መክፈታቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!