የሀገር ውስጥ ዜና

በአንበጣ መንጋ ሰብላቸው ለወደመባቸው አርሶ አደሮች ከ11 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ተዘጋጀ

By Tibebu Kebede

June 03, 2021

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ወሎ ዞን ባለፈው የመኸር በተከሰተ የአንበጣ መንጋ ሰብላቸው ለወደመባቸው አርሶ አደሮች ከ11 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ለመስጠት መዘጋጀቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ምክትል ኃላፊ አቶ አሊ ሰይድ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፈው ዓመት በዞኑ ሦስት ወረዳዎች የተከሰተ የአንበጣ መንጋ 11 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለማ ሰብል ሙሉ በሙሉ አውድሟል።

መንጋው ባደረሰው ጉዳት ከ10 ሺህ የሚበልጡ አርሶ አደሮች ከምርት ውጭ በመሆናቸው ለችግር መዳረጋቸውን ጠቁመው መንግስትና ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

አርሶ አደሮች በዘንድሮ መኸር የተሻለ ምርት በማምረት የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ እንዲችሉ መንግስት 11 ሺህ 839 ኩንታል ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በነጻ ማካካሻ ለመስጠት ማዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

ከምርትር ማሳደጊያው ውስጥ 4 ሺህ 873ቱ የስንዴና የጤፍ ምርጥ ዘር መሆኑን ጠቁመው በየወረዳው ለማሰራጨት ያላቸውን መሬት የማጣራትና የመጨረሻ የልየታ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

እንደየ መሬታቸው መጠን በነፍስ ወከፍ ከ15 ኪሎ ግራም እስከ ግማሽ ኩንታል ዘር ሊሰጣቸው እንደሚችል አመልክተው በቅርቡ የዘር ስራ እንዲጀምር አስታውቀዋል።

በዘንድሮ የመኸር የአንበጣ መንጋ ተከስቶ በሰብል ላይ ተመሳሳይ ጉዳት እንዳያደርስ ከወዲሁ አስፈላጊው የቅደመ ዝግጅት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የፌደራልና የክልል መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት መስጠታቸውን ጠቁመው ኬሚካል የሚረጩ አውሮፕላኖች እየተዘጋጁ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለምስራቅ አማራና ለአፋር ክልል በከፊል የሚያለግለግል አውሮፕላን ማረፊያ ኮምቦልቻ ላይ እየተመቻቸ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

በደቡብ ወሎ ዞን በዘንድሮው የመኸር ወቅት ከሚለማው 436 ሺህ ሄክታር መሬት ከ12 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!