የሀገር ውስጥ ዜና

19 ሺህ 739 ጥይቶችን ወደ ባህርዳር ሊያስገቡ የሞከሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

By Tibebu Kebede

June 03, 2021

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) 19 ሺህ 739 ተተኳሽ ጥይቶችን በባለ ሶስት እግር ባጃጅ ተሽከርካሪ ጭነው ወደ ባህር ዳር ሊያስገቡ የሞከሩ ሁለት ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን በጉምሩክ ኮሚሽን የባህር ዳር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ ስራ አስኪያጅ አቶ አለነ መሀሪ ለኢዜአ እንደገለጹት ግለሰቦቹ የቱርክ ሰራሽ ሽጉጥ ጥይቶቹን ከምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ ከደለጎ ከተማ ወደ ባህር ዳር ለማስገባት ሲሞክሩ ትናንት ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ግለሰቦቹ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 1-43622 አ.ማ በሆነ በባለ ሶስት እግር ባጃጅ ተሽከርካሪ ጭነው ወደ ባህርዳር ለማስገባት ሲሞክሩ በሻውራ ጉምሩክ ሰራተኞችና በፌደራል ፖሊስ ትብብር በተደረገ የኬላ ፍተሻ መያዛቸውን ተናግረዋል።

ተጠርጣሪ ግለሰቦቹ ለፖሊስ ተላልፈው ተሰጥተው ጉዳዩ እንዲጣራ እየተደረገ መሆኑንም አመላክተዋል።

ህገ ወጥ እንቅስቃሴ የማህበረሰቡንም ሆነ የሃገሪቱን ሰላም የሚጎዳ በመሆኑ ህብረተሰቡ መሰል ወንጀሎች ሲያጋጥሙት ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ ሀላፊነቱን እንዲወጣ ስራ አስኪያጁ ጥሪ አቅርበዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!