Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል እየተካሄደ ስላለው የሰብዓዊ ድጋፍና መልሶ ግንባታ ለዲፕሎማቶችና ለግብረሰናይ ድርጅቶች ማብራሪያ ተሰጠ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 26፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መንግስት በትግራይ ክልል እያካሄደ ስላለው የሰብዓዊ ድጋፍና መልሶ ግንባታ ተግባራት ለዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ ለአምባሳደሮችና ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት አካላት ማብራሪያ ተሰጠ፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በሰላም ሚኒስቴር አዘጋጅነት የዓለም አቀፍ ተቋማት አምባሳደሮችና ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች በተገኙት የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡

በምክክሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጨምሮ ሌሎች የስራ ሃላፊዎች በትግራይ ክልል በተለይም በአስቸኳይ ጊዜ ሰብዓዊ እርዳታ፣ በጤና፣ በትምህርትና በግብርና ዘርፎች እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ዙሪያ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

አቶ ደመቀ በትግራይ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ለመስጠት የተለያዩ የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍና ተቋርጠው የነበሩ አገልግሎቶችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ በርካታ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣትም የአጋር አካላት በተለይም የዓለም አቀፍ ተቋማትና ወዳጅ ሃገራት እገዛ ወሳኝ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

የሰላም ሚኒስትርና የአስቸኳይ ጊዜ ሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው በመጀመሪያ ዙር ድጋፍ 4 ሚሊየን ዜጎችን በሁለተኛና ሶስተኛ ዙር ደግሞ 4 ነጥብ 9 ሚሊየን ዜጎችን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል ትምህርት ቤቶችና ጤና ጣቢያዎች ተደራጅተው ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን፣ ለመኸር እርሻ ወቅት ደግሞ የማዳበሪያ የዘርና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ስርጭት ተደርጓል ብለዋል፡፡

በወንደሰን አረጋኸኝ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.