የሀገር ውስጥ ዜና

በኦሮሚያ ክልል 4 ነጥብ 2 ቢሊየን ችግኞች ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ነው

By Tibebu Kebede

June 03, 2021

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል የደን ልማትን ለማጠናከር በመጪው ክረምት 4 ነጥብ 2 ቢሊየን የተለያዩ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የገጠር ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ በተገኙበት በምሥራቅ ወለጋ ዞን ዲጋ ወረዳ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የችግኝ መትከያ ጉድጓድ ዝግጅት ተጀምሯል።

ዶክተር ግርማ አመንቴ በዚህ ወቅት እንደገለጹት በክልሉ የወልና የግል በሆነ 1 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ 4 ነጥብ 2 ቢሊየን የተለያዩ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

ለችግኝ ተከላው እየተዘጋጀ ያለው ቦታ በአባይ ተፋሰስ ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ የችግኝ ተከላው የውሃ ሀብትን ከደለል ለመጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው በመግለፅ ለስኬታማነቱ ህዝቡ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የምሥራቅ ወለጋ ዞን የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አስፋው ሐምቢሳ በበኩላቸው፥ በዞኑ በመጪው ክረምት ለሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ልማት የሚውሉ 312 ሚሊየን ችግኞች መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

ለተዘጋጁት ችግኞች መትከያ በህብረተሰቡ ተሳትፎ የጉድጓድ ቁፋሮ እየተካሄደ መሆኑን አመልክተው እስካሁንም 127 ሚሊየን ጉድጓዶች መዘጋጀታቸውን ኢዜአ በዘገባው አመላክቷል፡፡

ቀሪው በሂደት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው ችግኞቹ በዞኑ 17 ወረዳዎች በሚገኝ 101 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚተከሉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!